በኦሮሞና ሶማሌ ወሰኖች ላይ የተጀመረው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉ ተገለጸ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 4/2010) በኦሮሞና ሶማሌ ወሰኖች ላይ የተጀመረው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉ ተገለጸ።

በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሌ ክልል የተለያዩ ከተሞች ተፈናቅለው ወደ ሀረር መግባታቸው ታውቋል። ሁለቱ ክልሎች እየተወዛገቡ ነው።
ከሁለቱም ወገኖች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። ግጭቱ ወደ አጠቃልይ ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል እየተነገረ ነው።

የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አስተላልፈዋል። ይህ ግጭት በአገዛዙና በህዝብ መካከል ብቻ መሆኑን በሶማሌ እና ኦሮሚያ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በኢሳት በኩል መልዕክት እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል።
የሁለቱ ክልሎች መንግስታት እየተወነጃጀሉ ነው። ሁለቱም ወገኖች በየፊናቸው የሚያሰራጯቸው መልዕክቶች ግጭቱን ከማብረድ ይልቅ እንዲባባስ ምክንያት መሆኑም እየተነገረ ነው።

ይሄን ያህል ዜጎች ሲገደሉና ከሚኖሩበት ተባረው ሲወጡ በዝምታ እየተመለከተ ያለው የህወሃት መንግስት ለ26 አመታት የተከተለው የዘር ፖለቲካ ውጤት ነው የሚለው ድምዳሜ በብዙ ወገኖች ዘንድ እየተሰጠ ነው።
ለኢሳት የሚደረሱ መረጃዎች አሰቃቂ በመሆናቸው ለህዝብ ደህንነት ሲባል እንዳይተላለፉ መደረጋቸው ተገልጿል።

ባለፉት ሶስት ቀናት ከሶማሌ ክልል የተለያዩ ከተሞች በተለይም ከጂጂጋና ውጫሌ በመታወቂያቸው በሰፈረ የብሄር ማንነት እየተለዩ የሚገደሉ፣ የሚታሰሩ የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር እየጨመረ መቷል።

ይህን በመስጋት ቤት ንብረታቸውን ትተው የተሰደዱ የኦሮሞ ተወላጆች ወደ አቅራቢያ የኦሮሚያ መንደሮች እየገቡ ሲሆን በሀረር ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ መድረሳቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኢሳት ዛሬ በደረሰው መረጃ በሺ ዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከጅጅጋ በመውጣት ላይ ናቸው።

እስከ 12 ሺ የሚሆኑት ከሶማሌ ክልል እንደሚፈናቀሉ አንድ ባለስልጣን ለዘጋቢያችን ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹ በሽሽት ላይ እያሉ በመንገድ ላይ ግጭት ተከስቷል ተብሏል። ስለደረሰው ጉዳት ግን ዝርዝር መረጃ እየጠበቅን ነው።

ጥቃቱን እየፈጸሙ ያሉት የሶማሌ ልዩ ሃይል አባላት መሆናቸውን ተፈናቃዮች ይናገራሉ።

በሶማሌ ተወላጆች በኩልም ግድያና መፈናቀል እንደደረሰባቸው የሚገለጹ መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ በሶማሌ ልዩ ሃይል የጭካኔ እርምጃ የተቆጡ የኦሮሞ ተወላጆች ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ግጭት ተፈጥሮ 18 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል። ከእነዚህም ውስጥ 12ቱ የሶማሌ ተወላጆች መሆናቸው ተገልጿል።

ዛሬ በሃረር ተቃውሞ መካሄዱ ተሰምቷል። ሸዋ በር እና ፈረስ መጋላ አካባቢ የአጋዚ ወታደሮች አንድ ሰው መግደላቸው የተገለጸ ሲሆን ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ውጥረት መንገሱን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
በድሬደዋም እንዲሁ ግጭት እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን ስለደረሰው ጉዳት ግን የታወቀ ነገር የለም።

ሶማሌላንድ በተባለችው ሀገር የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት በመፈጸም ላይ መሆኑን ዘግይቶ የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ የኦሮሞ ተወላጆች በሶማሌላንድ መገደላቸውንም ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል ለኢሳት በስልክ፣ በኢሜይና በፌስቡክ ከሀገር ቤት በተለይም በሶማሌና ኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን በርካታ መልዕክቶች እየደረሱ ሲሆን ህዝቡ ከማንኛውም የእርስ በእርስ ግጭት ራሱን እንዲጠብቅና እንዲከላከል የሚጠይቁ ናቸው።

ይህ የህወሀት መንግስት ከህዝብ ጋር የገባበት ግጭት እንጂ በኢትዮጵያውያን መሀል የተፈጠረ አይደለም የሚለው መልዕክት በሁለቱም ክልሎች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተላለፉ ናቸው።