(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 27/2010)
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየወሰደ ያለው ርምጃ በውጭ ግንኙነቱ ላይ ትልቅ ፋይዳ አለው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ እንዳለው የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ይፈታሉ መባሉ ግን በውጭ መንግስታት ተጽእኖ አይደለም ሲል አስተባብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም እንዳሉት የሀገሪቱ የደህንነት ምንጭ ከውስጥ ጥንካሬ የሚመነጭ ነው።
ሆኖም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተወሰደ ያለው ርምጃ ግን በውጭ ግንኙነት ላይ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
እስረኞቹ እንዲፈቱ የተወሰነው የውጭ ሃያላን መንግስታት ተጽእኖ በመፍጠራቸው ነው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ማስተባበያ ሰጥተዋል።
በአውሮፓ ሕብረት፣በእንግሊዝና በአሜሪካ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ግፊት ሲደረግ መቆየቱ ይታወሳል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሒውማን ራይትስዎች በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ ክፉኛ በመኮነን መግለጫ ሲያወጡ ቆይተዋል።
እናም ይህ ሁሉ ተጽእኖ የሕወሃትን አገዛዝ እስረኛ እንዲፈታ አላስገደደውም ብለዋል የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ አቶ መለስ አለም።
አቶ መለሰ በውጭ ጉንኙነቱ ላይ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ያሉት የኢሕአዴግ መግለጫ ከምን አኳያ እንደሆነ ግን ግልጽ ማብራሪያ አልሰጡም።
እርሳቸው እንደሚሉት ርምጃው ሰላምና መረጋጋትን ስለሚያመጣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ይስባል ቢሉም እስረኞቹ ግን በተጽእኖ እንዲለቀቁ አልተወሰም ብለዋል።
በአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ በቅርቡ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ዙሪያም መምከራቸው አይዘነጋም።