ሰኔ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ለሕዝበ ሙስሊሙ ወቅታዊ ጥያቄዎች መፍትሔ ለማፈላለግ የተመረጠው ኮሚቴ ያሳለፋቸውን ሒደቶችና ለመንግስትና ለባለድርሻ አካላት ያስገባቸው ደብዳቤዎች ያሰባሰበ 103 ያህል ገጽ የያዘና “እውነቱ ይህ ነው” የሚል ርዕስ የተሰጠው መጽሐፍ ዛሬ ለሕዝብ ይፋ ሆነ፡፡
የሕዝበሙስሊሙን ወቅታዊ ጥያቄዎች መፍትሔ ለማፈላለግ የተመረጠው ኮሚቴ ባሳተመው በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ የሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲመለሱ ኮሚቴው የሄደባቸውን መንገዶች፣የተጻጻፋቸውን ደብዳቤዎች
ያካተተ ነው፡፡
መጽሐፉ አምስት ወራት የዘለቀው የሙስሊሙ ጥያቄዎች አሁንም ምላሸ ከማግኘት ይልቅ ጥያቄ አቅራቢ ወገኖችን እንደሰላም አደፍራሸና ጸረ ሰላም ኃይል የመፈረጅ አዝማሚያዎች እየታዩ መሆኑን ይዘረዝራል፡፡
በመጽሐፉ ይፋ ከሆኑት መረጃዎች መካከል ኮሚቴው ላቀረባቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሸ አለማግኘቱን በመጥቀስ ለአቶ መለስ ዜናዊ ጋር የውይይት መድረክ እንዲመቻችላቸው ለጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ መጋቢት 3 ቀን
2004 ዓ.ም ያቀረቡት ደብዳቤ ይገኝበታል፡፡በዚሁ ደብዳቤ የአገሪቱ 33 በመቶ የሚሆነውን የህብረተሰብ ክፍል የሚወክለው የኢትዮጽያ እስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤት (መጅሊስ) ተገቢውን ሕጋዊ ሰውነት የሌለውና በሕዝብ
ባልተመረጡና ዕውቅና በሌላቸው አመራሮች መመራቱ ሕዝበ ሙስሊሙን እያስከፋው እንደሚገኝ ይጠቅሳል፡፡
መጅሊሱ የሕገመንግስቱን ድንጋጌዎች በሚጻረር፣በኢህአዴግ መንግስት ታሪክም ባልታየ፣በእስልምና አስተምህሮ መርሆዎች ባልተደነገጉና ፍጹም መሰረት በሌላቸው በእስልምና ስም በመሪ ተቋማችን አስተባባሪነት ከእስልምና ውጪ የሆነ ባዕድ
እምነት ሕዝበ ሙስሊሙን በመጋት ቁጣና አለመረጋጋት እየቀሰቀሱ ይገኛሉ፡፡ይህ ዓይን ያወጣ በደል ያስቆጣው ሙስሊሙ ህ/ሰብ በተደጋጋሚ በተለያየ አግባቦች የቅሬታውን ትክክለኛ ምንጭና ገጽታ ለሚመለከተው የመንግስት አካል
በወከላቸው ኮሚቴዎች አማካኝነት በሰላማዊ መንገድ አቅርቦ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡
መረጃው አያይዞም በዚሁ መሰረት ለተለያዩ የታችኛው የመንግስት አስተዳደር እርከን ቅሬታችንን ከማቅረብ ባሻገር በፌዴራል ደረጃ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ቅሬታችንን አቅርበን በ26/06/2004 በተሰጠን ቀጠሮ መሰረት ሰፊ ውይይት ተካሒዷል፡፡ ይሁን እንጂ በዕለቱ የተሰጠው ምላሸ በተጨባጭ የህብረተሰቡን ትክክለኛ የቅሬታ ምንጭ ያላገናዘበና ለችግሮቹም መፍትሔ ያልሰጠ በመሆኑ በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
ምላሹን አስመልክቶ ሚኒስቴሩ በወቅቱ ለመገናኛ ብዙሃን የሰጠው መግለጫ ከውይይቱ መንፈስ ውጪና የጋራ መግባባት ያልተደረሰበት መሆኑን ማስረጃ በማጣቀስ ኮሚቴው ቅሬታውን በጹሑፍ አስገብቷል፡፡በመሆኑም የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ሙስሊሙ አቤቱታውን ለላይኛው የመንግስት እርከን ቀርቦ ተገቢውን መፍትሔ እንዲሰጠው አጥብቆ ይጠይቃል ሲል ያትታል፡፡
ለአቶ መለስ የተጻፈውና ምላሸ ያላገኘው ደብዳቤ አያይዞም በመጅሊሱ ሳይሆን እሱን በሚመሩ ግለሰቦች የግል ፍላጎት ምክንያት ከሃይማኖቱ መርሆዎች ውጪ በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የሚጫንበት ተደጋጋሚ በደል የሚፈጥረው ቁጣና ተቃውሞ በሂደት በሃገራችን ሰላም፤ደህንነትና ጸረ ድህነት ትግል እንቅፋት ስለሚሆን መንግስት ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ የተጋረጠውን ችግር እንዲፈታ ሲል ይጠይቃል፡፡
ከዚህ በመነሳትም በኢትዮጽያ ሙስሊሞች ወቅታዊ ጥያቄዎች ይዘት ላይ ለመወያየትና የጋራ የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ ለመመካከር የውይይት መድረክ እንዲመቻችላቸው በወከላቸው ህዝበ ሙስሊም ስም ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም ኮሚቴው ሚያዝያ 12 ቀን 2004 ዓ.ም በድጋሚ ለ አቶ መለስ ዜናዊ በላከው ደብዳቤ ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳቸውን የመብት ጥያቄዎችን ተንተርሶ በአንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት እየታየ ያለውን ህዝብን የማሸማቀቅና የማዋከብ ተግባር እንዲያስቆሙላቸው ጠይቋል፡፡
ግንቦት 2 ቀን 2004 ዓ.ም ለህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መፍትሔ ለማፈላለግ የተቋቋመው ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለእስር የተዳረጉ ሙስሊሞች እንዲፈቱ፣ማሰፈራራቶችና የኃይል እርምጃዎች እንዲቆሙ፣ዴሞክራሲና
እውነተኛ ሰላም ከማንም በላይ ለህዝበ ሙስሊሙ ብቸኛ የድል መስመሮች መሆናቸውን በማስታወስ ወደ ብጥብጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ድርጊቶችን በመስጊዶችም ሆነ በማንኛውም ቦታ እንዳይከሰቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡
ይኽው መጽሐፍ በመደምደሚያው ከሙስሊሙ ሰላማዊ ጥያቄዎች ጋር በተገናኘ ከፌዴራል እስከ ታችኞቹ የመንግስት አስተዳደር መዋቅሮች ሰላማዊ ጥያቄውን ከዜጎች ሰላምና ደህንነት ጋር በማቆራኘት በማስፈራራትና በማሸማቀቅ ጥያቄውን ለማፈን የሚደረጉ ጥረቶች ኢ-ሕገመንግስታዊ በመሆናቸው በአስቸኳያ እንዲቆሙ ጠይቋል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙ ባለፉት አምስት ወራት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ካቀረባቸውና ምላሸ ከተነፈጋቸው ጥያቄዎች መካከል መጅሊስ ይፍረስና ፍትሐዊ ምርጫ ይደረግ፣አወሊያ ት/ቤት በቦርድ ይተዳደር፣በመጂሊሱ የሚሰጠው የሃይማኖት አስተምህሮ እንዲቀር የሚጠይቁ ናቸው፡፡
በያዝነው ወር መንግስት ምርጫ በየቀበሌው እንደሚካሄድ ይፋ ቢያደርግም ምርጫው ነጻና ገለልተኛ ያልሆነና የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያለበት ነው በሚል በኮሚቴው ዘንድ ተቀባይነት ማጣቱ ግለቱን ጨምሮታል፡፡
በትናንትናው እለት የተበተበተነው ወረቅት ህዝበ ሙስሊሙ ለ6 ወር ያህል “በህገ-ወጥ መንገድ መጅሊስን የወረሩት አመራሮች ይውረዱና የእምነት ተቋም መሪዬን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ልምረጥ! የፍትህ ያለህ!” ሲል ቢልም ህዝብን ለማዘናገት ይወርዳሉ የሚል ወሬ ከማናፈስ ውጪአሁንም ድረስ በወንበራቸው ላይ ተደላድለው ይገኛሉ ብሎአል።
ለይስሙላ እና ለማስመሰል በየምርጫ ጣቢያው ጣል ጣል ከሚደረጉት ጥቂቶች በቀር በአጠቃላይ እጩውም፣ አስመራጩም፣ ተመራጩም፣ ታዛቢውም፣ ድምጽ ቆጣሪውም፣ ቅሬታ ሰሚውም ሁሉም የአህባሽን አስተሳሰብ የሚያራመዱ መጅሊሶችና አጋሮቻቸው እንዲሆኑ እየተደረገ ነው የሚለው በራሪ ወረቀት፣ ይህ ሁሉ ህዝበ ሙስሊሙ የማይቀበለው ህገ-ወጥና ፀረ-ህገመንግስት ተግባር ነውና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ ሊቆም ይገባዋል ብሎአል።
ምርጫው ባልተመረጡ ህገ-ወጦች መጅሊሶች ሳይሆን ህዝበ ሙስሊሙ በየአካባቢው በሚሰይማቸው አስመራጮች አማካኝነት ሊከናወን ይገባል የሚለው መግለጫ፣ ሙስሊሙ አስመራጮችን በመሰየም ምርጫ እንዲያካሂድ ጠይቋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide