ጥቅምት ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መጤ አረሙ ከሸፈነው መሬት ሁለት ሺህ ሄክታር በሩዝ ማሳ ላይ ሲሆን ቀሪው በኃይቁና በዙሪያው በሚገኙ ውሃ አዘል መሬት ላይ መሆኑን ተገልጿል፡፡ አረሙ በደንቢያ፣ በጎንደር ዙሪያ፣ በሊቦ ከምከም፣ በፎገራና በደራ ወረዳ በሚገኙ 16 ቀበሌዎች በፍጥነት እየተዛመተ እንደሆነም ታውቋል።አረሙን ለማጥፋት ሲሞከርም በሦስት ሳምንታት ራሱን መልሶ የሚተካ መሆኑና በውሃው ላይ በመንሳፈፍ በንፋስ ሃይል እየተገፋ የሚራባ በመሆኑ የመከላከል ስራውን ፈታኝ እንዳደረገው ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች ገልፀዋል።
አረሙ በቀጣይም ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እየፈሰሰባቸው ለሚገኙ በጣና ዙሪያ እየተገነቡ ላሉ የመስኖ ግድቦችና ኤሌክትሪክ ሃይል ግድብ ስጋት ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች አስታውቀዋል።በሊቦ ከምከም ወረዳ አረሙ በሦስት ቀበሌ በአንድ ሺህ 556 ሄክታር የወል መሬትና የሩዝ ሰብል ማሳ ላይ መከሰቱ ተገልጿል። በካብ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች እንደተናገሩት አረሙ በሩዝ ማሳቸው ላይ ከተከሰተ ጀምሮ በየቀኑ በመሰብሰብ የማስወገድ ስራ ቢያከናውኑም የሩዝ ምርታቸው በመቀነስ ተጽኖ እያደረሰ ነው። የእንስሳቱን የግጦሽ ቦታን ሙሉ በሙሉ በመውረር መኖውን በማጥፋቱ እንስሳቶቻቸው ለረሃብ እየተጋለጡ መሆኑን ገልጸው እንስሳቱ አረሙን ቢመገቡም ለበሽታ እያጋለጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
አረሙ የውሃውን ሽታና ጣዕም በመቀየር በጤናቸው ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ የቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደሮች ተናግረዋል። እንዲሁም በአካባቢው በስፋት ይገኝ የነበረው የአሳ ምርት እየቀነሰ ከመምጣቱም በላይ ተፈጥሯዊ ጣዕሙም የመለዋወጥ ባህሪ እያሳየ እንደሆነ አመልክተዋል።
መጤ አረሙ ከአንድ ዓመት በፊት 20 ሺህ ሄክታር በሀይቁና በገጸ ምድር ተከስቶ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተደረገ ርብርብ ከ95 በመቶ በላይ ማጽዳት ተችሏል በሚል ከአንድ ዓመት በፊት የገዢው መንግስት ሚዲያዎች ቢናገሩም ፣ በጣና ሃይቅ ላይ ብቻ ከ46 ሽህ ሄክታር በላይ ተስፋፍቶ እንደሚገኝ ባለሙያዎች ለኢሳት ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ የግል ሚዲያዎችና አለም አቀፍ ጸሃፊዎች ከአመታት በፊት ሲያሳስቡት እንደነበር የሚናገሩት የአካባቢው ተቆርቋሪዎች በፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ በ2004 ዓ.ም በጸሃፊ መምህር ደረጀ መላኩ በተጻፈው ʻ የጣና ሃይቅ ብክለት ከየት መጣ? ʼ በሚል ርእስ ያስነበበውን ያስታውሳሉ፡፡ ከአመታት በፊት ሄንረይ ኒኦንዶ የተባሉ ጸሃፊ ስለ አረሙ ወረራ አስከፊነት ልዩ ልዩ መረጃዎችንና ተመራማሪዎችን በማነጋገር Africa science ላይ በዚሁ መጤ አረም የነዋሪዎች ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ጠቅሰዋል። በአሁኑ ሰአት በስፋት በየአካባቢው በሚደረጉ የድርጅቱ ስብሰባዎች ፋታ ያጣው ገዢው መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዳልሰጠው ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡