ጥቅምት ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሆለታ ገነት የሚገኘው የሼከ አላሙዲ ንብረት የሆነው “ኢትዮ ድሪም” የአበባ እና የእንጆሪ ሰራተኞች ጥቅምት 21 እና 22 ከፍያ ተፈጽሞላቸዋል። ሰራተኞች ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው ለኢሳት ባስተዋቁ በቀናት ውስጥ እንደተከፈላቸው ቢገልጹም፣ አሁንም ከሰራተኞች ማመላለሻ መኪናና ከጤና ጋር የተያያዙ ችግሮችን እያነሱ ነው። ድርጀቱ ለሰራተኛ ማመላለሻ /ሰርቪስ/ እና ለምርት ማጓጓዣ የተከራያቸው መኪኖች የአገልግሎት ክፍያ ሳያገኙ ከ7 ወራት በላይ ያለፋቸው ሲሆን፣ ካለፈው ወር ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው ሰራተኛው ከሚከፈለው አነስተኛ ገንዘብ እየቆጠበ ለትራንስፖርት በቀን እስከ አስር ብር ለማውጣት ተገዷል። ሰራተኞች እንደሚሉት አብዛኛው ሰራተኛ 600 ብር ወርሃዊ ክፍያ የሚያገኝ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 150 ብር ለቤት ኪራይ፣ 260 ብር ለትራንስፖርት ከፍሎ በወር ከ200 በታች በሆነ ብር ቤተሰቡን ያስተዳድራል።
በአበባ እርሻ ውስጥ የተከሰተው የአበባ በሽታ ለጤናቸው አስጊ መሆኑን የሚናጉት ሰራተኞችን በተለይም “ማይቲ” የተባለው በሽታ ሰውነትን የሚያሳክክ ከመሆኑም በተጨማሪ የጤና ባለሞያዎች ሁኔታውን እንዲያጠኑና እዲያሳውቁ ከሰራተኞች የተውጣጡ አባላት ለጤና ቢሮ አቤቱታ ለማስገባት ለ ጥቅምት 24 2007 ቀጠሮ መያዙን ሰራተኞች ለኢሳት ገልጸዋል።