(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 12/2010) ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል 50ኛ አመት በአል ተጋብዞ ወደ ሆላንድ አምስተርዳም ሊያመራ ሲል በቦሌ አይሮፕላን ማረፊያ የታገደው እስክንድር ነጋ ፓስፖርቱ ተመለሰለት።
እስክንድር ነጋ በደህንነት ሰራተኞች ፓስፖርቱን ከተቀማ በኋላ ትላንት ወደ አምስተርዳም እንዳይበር ተደርጎ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ፓስፖርቱ ተመልሶለት ነገ በሚከበረው 50ኛ አመት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል በአል እንዲሄድ አገዛዙ መፍቀዱን ለማወቅ ተችሏል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በሰብአዊ መብት ተከራካሪነቱና በዲሞክራሲ አቀንቃኝነቱ በተደጋጋሚ ጊዜ በመታሰር ከፍተኛ ስቃይና እንግልት ከደረሰበት በኋላ በቅርቡ ከእስር መለቀቁ ይታወሳል ።
እስክንድር ነጋ እስር ቤት ውስጥም ሆኖ በርካታ አለምአቀፍ ሽልማቶችን የተቀናጀ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነው።
በቅርቡ ከእስር ከተፈታ በኋላ እንደገና ከሌሎች ጓደኞቹና የሙያ አጋሮቹ ጋር ታስሮ የተለቀቀው እስክንድር ነጋ በነገው እለት በኔዘርላድስ አምስተርዳም በሚከበረው የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ቡድን አምነስቲ ኢንተርናሽናል 50ኛ አመት በአል ላይ እንዲገኝ ተጋብዞ ነበር።
ይህንኑ መሰረት በማድረግም ትላንት ምሽት ወደ አምስተርዳም ሊያመራ ሲል ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የይለፍ ፈቃድ ካገኘ በኋላ በደህንነት ሰራተኞች ፓስፖርቱን ተቀምቶ ወደ ውጭ እንዳይበር ታግዷል።
“እቃዬን አስገብቼ የይለፍ ፈቃድ ካገኘሁ በኋላ አንዲት ሴት ፓስፖርቴን ተቀብላ ኢሚግሬሽን ዋናው ቤሮ አናግር” በማለት መልሳኛለች ብሏል እስክንድር ስልሁኔታው ሲያብራራ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስክንድር ነጋ ፓስፖርት መመለሱን ለቢቢሲ አማርኛ ዘና ዝግጅት ክፍል ገልጿል።
ምናልባትም እስክንድር ከሐገር እንዲወጣ ከተፈቀደለት ነገ በሚካሄደው 50ኛው አመት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል በአል ላይ ሊደርስ ይችላል።