እስክንድር ነጋ ጥቅምት 27 ጠቅላይ ፍ/ቤት ይቀርባል

ጥቅምት ፲፫ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የ18 አመት ጽኑ እስራት የተፈረደበትና ላለፉት 13 ወራት በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኘው፤ ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ በመጭው ጥቅምት 27 በጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ይግባኙ እንደሚደመጥ ኢትዮጽያን ሪፖርተር ዘገበ::

በ2001 አም በወጣውና አፋኝ እንደሆነ የሚተቸውን ጸረ ሽብር ህጉን በመጣስ የተከሰሰው እስክንድር ነጋ፤ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ያለበትን የህግ ስህተቶችና የማስረጃ ድክመት ጠቅሶ በመሰረተው ይግብኝ፤ በሽብርም ይሁን በአመጽ እንዳልተሳተፈ፤ በሰላማዊ መንገድና ህገመንግስቱን መሰረት አድርጎ ብቻ ይንቀሳቀስ እንደነበር በይግባኙ ላይ አመልክቶል::

ከፍተኛው ፍ/ቤት ለውሳኔ በሚያመቸው መልኩ የምስክሮችን ቃልና ማስረጃ እየጠየቀ የተሳሳተ ውሳኔ እንዳስተላለፈ የተናገረው እስክንድር ነጋ፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያለበቂ ማስረጃ የተፈረደበት ፍርድ እንዲቀለብስና በነጻ እንዲያሰናብተው ይግባኝ ብሎል::

እስክንድር ነጋ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ይግባኝ ሲል፤ የሚከራከርበት ቀን ጥቅምት 27 የተወለደበትና 43 ኛ አመቱን የሚያከብርበት ቀን መሆኑን ለማወቅ ተችሎል::

በአሜሪካን ሀገር ትምህርቱን የተማረውና ከ18 አመት ቆይታ በኋላ ወደ እናት አገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶ በጋዜጠኝነት ሙያ የተሰማራው እስክንድር ነጋ፤ ባለፉት 20 አመታት ከ8 ጊዜ በላይ የታሰረ ሲሆን፤ ባለፈው አመት የ18 አመት ጽኑ እስራት ተፈርዶበት በቃሊቲ እንደሚገኝ ይታወቃል::

እስክንድር ነጋ የፔን አሜሪካ ተሸላሚ ነው:: ባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል ደግሞ የአለም አቀፉ የሴቶች ሚዲያ ፎረም ተሸላሚ ናት:: ልጃቸው ናፍቆት እስክንድር ሁለቱ ባልና ሚስት ታስረው ቃሊቲ በነበሩበት ግዜ ነው ነበር የተወለደው። እስክንድር ለመጨረሻ ግዜ የታሰረው ልጁን ከትምህርት ቤት ወደቤት ሲመልስ ነበር።

እስክንድር ነጋ ለጠቅላይ ፍ/ቤቱ ይግባኝ ቢልም፤ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የህግ አማራጮች አሟጦ ከመጨረስ አንጻር እንጂ፤ ፍትሕ ጠብቆ አይደለም ሲሉ የጠቅላይ ፍርድቤቱን የቀድሞ ውሳኔዎች እንደማስረጃ የሚያነሱ ሰዎች ይናገራሉ።

ባለፈው ሳምንት የጠ/ፍ/ቤቱ ሰበር ሰሚ ችሎች፤ ወደ 20 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤንና የሴቶች የሕግ ባለሙያ ማህበር ገንዘብ እንዲታገድና እንዲወረስ የበታች ፍ/ቤቶች የወሰኑትን ውሳኔ መሰረታዊ ሕግ ስህተት የለበትም ብሎ ማጽናቱ ይታወሳል።