እስራኤል የመጨረሻዎቹን ቤተ-እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ልታጓጉዝ ነው

ሐምሌ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የእስራኤል መንግስት 2 ሺህ 200 ቤተ እስራኤላውያንን እ.ኤ.አ እስከ ማርች 2014 ድረስ ከኢትዮጵያ  ለማንሳት እንዳቀደ አስታወቀ።

እነኚሁ ከኢትዮጵያ የሚጓጓዙት ቤተ እስራኤላውያን  የመጨረሻዎቹ እንደሆኑ የገለፀው የእስራኤል ካቢኔ፣ የሚያስፈልጋቸውን መጠለያና ሌላም ነገር ለማሟላት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የመደበ ሲሆን፣ በየወሩ 250 ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ለማምጣት እንዳቀደ ገልጿል ።

በተለምዶ “ፈላሻ-ሙራ” በመባል የሚታወቁት እነኚሁ ኢትዮጵያዊያን ይሁዲዎች፣ ወደ እስራዔል የመጓዝ ተስፋን ሰ ንቀው በተለይም ባለፉት አስር ዓመታት፣ ጎንደር ውስጥ በከፍተኛ ችግር ላይ እንደነበሩ የጠቆመው የእስራዔል መንግስት፣ ከረጅም ጊዜ በኋላ እነርሱን ወደ እስራኤል ለማጓጓዝ ከውሳኔ ላይ የተደረሰው በተለይም በእስራዔል የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ አባላት እና አለም አቀፍ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ጫና እና ግፊት እንደሆነ ሳይጠቅስ አላለፈም።

ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ብቻ 120 ሺህ ፈላሻ ሙራዎች ከኢትዮጵያ ወደ እስራዔል የገቡ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል አብዛኞቹ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ሆነው መገኘታቸው በርካታ ችግር ያስከተለባቸው ነገር ነበር።

ሆኖም ከነኝህ ውስጥ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሃይማኖታቸውን ወደ ይሁዲ እምነት እንዲቀይሩ የተደረገ ሲሆን፣ አሁን የሚጓጓዙት ቤተ እስራኤላውያንም ከምንም ነገር በፊት በዚሁ መንገድ ማለፍ እንደሚኖርባቸው ይኸው የዜና ዘገባ ይጠቁማል።

ምንም እንኳን በእስራዔል በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ፈላሻ ሙራዎች ላይ ከዘረኝነት ጋር የተያያዘ አሳዛኝ መገለልና በደል እንደሚደርስባቸው በርካታ የዓለማችን ሚድያዎች በተለያየ ጊዜ ቢያስተጋቡም፣ ይህ ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እየተሻሻለ እንደመጣ እየታዩ ያሉት እውነታዎች ይጠቁማሉ።

በዚህ በኩል በተለይም የእስራዔል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን  ናታኒያሁ የኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤላውያን አጠቃላይ ሁለንተና በተደጋጋሚ ከጎበኙ በኋላ ባለፈው ሚያዝያ ወር ለካቢኔያቸው ያደረጉት ንግግር የሚጠቀስ ነው።

ናታኒያሁ በዚሁ ጥልቅ ስሜት በተጎናፀፈ ንግግራቸው፣ መንግስታቸው  የቤተ እስራኤላውያኑን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከጎናቸው በመቆም በብርቱ እንደሚሰራ በመግለጽ፤ የኢትዪጵያውያኑ ቤተ እስራዔላውያን ሕፃናት ልጆች ከሌላው ማሕበረሰብ ተነጥለው እንዲማሩ እየተደረገ ያለውን አሳፋሪ አድልዎ አጥብቀው ኮንነዋል።

በወቅቱ ለእስራኤል ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክትም  “ከእንግዲህ በኋላ በእስራኤል ምድር ለዘረኝነት ቦታ የለንም” በማለት የመንግስታቸውን አቋም በግልጽ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በእስራኤል ከሚኖሩት ፈላሻ ሙራዎች መካከል 80 ሺህ ያህሉ የተወለዱት ኢትዪጵያ ውስጥ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 40 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ እስራኤል ውስጥ መወለዳቸው ታውቋል።

ሆኖም ምንም እንኳን የእስራኤል መንግሥት ቤተ እስራኤላውያኑን ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ትስስር ለማቆም በልዩ ልዩ መልኩ ጥረት ቢያደርግም፣ እስከአሁን እንዳልተሳካለትና አብዛኞቹም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ስር የሰደደ ቁርኝት ተበጥሶ እንዳይቀር ብርቱ  ጥረት እንደሚያደርጉ በገሃድ እያየነው ያለ እውነታ ነው።

ከኢትዮጵያ ከሄዱት ቤተ እስራኤላውያን መካከል ተሳክቶላቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ሲኖሩ፣ በውትድርናው መስክ ተቀጥረው እያገለገሉ ያሉትም በርካቶች ናቸው።  የእስራዔል መንግስት ባለፈው የካቲት ወር፤ ወይዘሮ በላይነሽ ዝቫዲያ  የተሰኙ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለዱ ቤተ እስራኤላዊ፣ በኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር አድርጎ መሾሙ ይታወሳል ሲል ቅዱስ ሃብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide