ሚያዚያ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሪፖርተር እንደዘገበው ከፌደራል ጀምሮ እስከ ክልሎችና ወረዳዎች ድረስ በርካታ ችግሮች የሚስተዋልበት የገንዘብ አስተዳደር እንዲያሻሽል ጥሪ ያቀረቡት ዋነኞቹ የኢትዮጵያ ለጋሽ አገራት፣ ችግሮቹንና አሳሳቢነታቸውን የለዩ የተለያዩ ጥናቶችን በማከናወን ሁሉንም የፌደራል፣ የክልልና የወረዳዎች የፋይናንስ አስተዳደር ኃላፊዎች አዲስ አበባ ላይ በመሰብሰብ፣ በችግሮቹና መፍትሔዎች ዙርያ ባለፉት ሁለት ቀናት ውይይት አድርገዋል፡፡
የቡድኑ አስተባባሪና በዓለም ባንክ የአፍሪካ የፋይናንስ አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት ሚስተር ፓርሚንደር ፒኤስ ብራር ለጋዜጣው እንደገለጡት መንግሥት በዚህ የገንዘብ አስተዳደር ዘርፍ ለሚስተዋሉ የተለያዩ ችግሮች ትኩረት ቢሰጥም፣ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ባለመቀረፉ ውይይቱን ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ታክስ አሰባሰብ ስርአት እንዲሻሻል ቡድኑ የጠየቀ ሲሆን የኢትዮጵያ የታክስ ገቢ ለአገሪቱ ጠቅላላ ምርት እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ መሆኑ ዕድገቱን ለማስቀጠል እንከን ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ሌሎች መሻሻል አለባቸው የተባሉት ጉዳዮች የውጭ ኦዲት ቁጥጥር የጥራት ደረጃ እና የሽፋን አድማስ ፣ የመንግሥት የግዥ አፈጻጸም ሥርዓት እና የተወካዮች ምክር ቤት በፋይናንስ አስተዳደር ረገድ ያለው ሚና ይገኙበታል፡፡
በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ሪፎርም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙሳ መሐመድ ችግሮቹ መኖራቸውን አምነዋል።