ኤርትራ በሶማሊያ ሰላም እንዳይኖር እየሰራች ነው ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤክስፐርቶች አስታወቁ

ሐምሌ ፲፩(አስራ አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሪዩተርስ ሚስጢራዊ ሰነድ አገኘሁ በማለት ባወጣው ዘገባ ምንም እንኳ የኤርትራ መንግስት የሶማሊያ ታጣቂ የሆነውን አልሸባብን አልደግፍም ቢልም ፣ ቡድኑ ግን ኤርትራ ታጣቂውን ሀይል መደገፉዋን በመቀጠሉዋ የተጣለባት ማእቀብ እንዳይነሳ አቤት ብሎአል።  ኤርትራ አብዲ ኑር ሰኢድ በተባለ የሶማሊያ ተወላጅ በኩል እርዳታ እንደምታደርግ ማረጋገጡን ቡድኑ ጠቅሷል።

በቀረበባት ክስ ላይ ኤርትራ አስተያየቱዋን አልሰጠችም። ሩሲያ እና ጣሊያን በመርማሪ ቡድኑ የቀረበውን ሪፖርት ተቃውመውታል።

ረዩተርስ የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ሩሲያ ሪፖርቱ እንዳይታተም የተቃወመችው ፣ ጥናቱ ሚዛናዊ ያልሆነና በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ የተደረሰ ድምዳሜንና አስተያየትን ያልያዘ ነው በሚል ነው።

ጣሊያን በበኩሉዋ ሪፖርቱ አሳሳች እና ማስረጃ የሌላቸውን መረጃዎች የያዘ ነው ብላለች። ሪፖርቱ ለማእድን ስራ የተላከ የጣሊያን ሄሊኮፕተር በወታደራዊ ካምፕ አካባቢ በመታየቱ ምናልባትም የጦር መሳሪያ ይዞ ሊሆን ይችላል በማለት የገለጸውን ጣሊያን ውድቅ አድርጋዋለች። ጣሊያን ለኤርትራ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ድጋፍ አላደረገችም ስትል የጣሊያን የተመድ አምባሳደር ተናግረዋል።