ኢንተርናሽናል ክርስቲያን ኮንሰርን በእስረኞች ላይ ጉዳት እንደተፈፀመባቸው ገለፀ

መጋቢት ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ባለፈው ታህሳስ  ወር በሳዑዲ አረቢያ  የገናን በዓል ለማክበር በመሰባሰባቸው ለእስር የተዳረጉት 35 ኢትዮጵያውያን አብረዋቸው በታሰሩ ሌሎች እስረኞች ከፍ ያለ ጉዳት እየተፈፀመባቸው መሆኑን ኢንተርናሽናል ክርስቲያን ኮንሰርን ገለጸ።

ጂዳ ውስጥ በብሪማን እስር ቤት ውስጥ  በከባድ ወንጀል ከተከሰሱ እስረኞች ጋር  ከታሰሩት ኢትዮጵያውያን አንዱ፦”ያሰሩን  በነፍስ ግድያ ከታሰሩ ወንጀለኞች ጋር ነው።እነዚህ እስረኞች አንድ ቀን በእኛ ላይ ጉዳት ሊያደርሱብን ስለሚችሉ የደህንነታችን ሁኔታ እጅግ አሣስቦናል።የ ሳዑዲ መንግስት ይፈታን ዘንድ ግፊት ማድረጋችሁን ቀጥሉልን” ሲል  ለዓለማቀፉ የክርስቲያን ጉዳዮች ተወካይ ተማጽኗል።

እስረኞቹን የጎበኙት የድርጅቱ  ልዑካን እንዳረጋገጡት፤በኢትዮጵያውያኑ እስረኞች ላይ እስካሁን ምንም ዓይነት ክስ አልተመሰረተም።

የድርጅቱ ተወካይ ጆናታን ራኮ ፤እስረኞቹ በተለይ በበቂ ምግብና  ህክምና አለማግኘት ሳቢያ አያያዛቸው እየከፋ መምጣቱን ነግረውናል ብለዋል።

በመሆኑም ድርጅቱ በዋሽንግተንና አካባቢው ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር   በመሆን  እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የፊታችን ማርች 26 ቀን ከረፋዱ 11 ኤ.ኤም ጀምሮ በዋሺንግተን ፣በኒው ሀምፕሻየር ጎዳና በሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት  የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርጉ አስታውቋል።

“የሳኡዲ ኤምባሲና መንግስት ጥያቄያችንን የምር አድርገው አልወሰዱትም።  ንፁሀን ኢትዮጵያውያኑን በመልቀቅ ፋንታ፤ ያልሆነ ምክንያት እየደረደሩ  ያለ ጥፋታቸው በ እስር ቤት ሊያቆዩዋቸው ይፈልጋሉ” ብለዋል- ከተቃውሞ ሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ አክቲቪስቱ አቶ ከባዱ በላቸው።

የኢንተርናሽናል ክርስቲያን ኮንሰርኑ ሚስተር ጆናታን በበኩላቸው ደጋፊዎቻችን የተቃውሞ ሰልፉን እንዲቀላቀሉ ጥረት እያደረግን ነው። የ ሳዑዲ መንግስት ኢትዮጵያውያኑን እስኪፈታ ድረስ ግፊታችንን አጠንክረን እንቀጥላለን” ብለዋል።

የታሳሪ ኢትዮጵያውያኑ ፎቶ ይፋ የሆነ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ሴቶችን የቤተሰብ ሀላፊዎች መሆናቸው ታውቋል።

ዓለማቀፍ ድርጅቶች ኢትዮጵያውያኑን ለማስፈታት  ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ባሉበት ጊዜ፤ በሳዑዲ የሚገኘው የ ኢትዮጵያ ኤምባሲና የኢትዮጵያ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር 45 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ለቤት ሠራተኝነት ወደ ሳዑዲ ለመላክና  በሪያድና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለ ዓባይ ግድብ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide