በአዲስ አበባ የሚገኙ መምህራን የስራ ማቆም አድማ አደረጉ አድማው ለሁለት ቀናት ይቆያል

መጋቢት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሃሙስ መጋቢት 13 ቀን 2004 ዓ.ም  ለዓመታት ስንታገልለት በነበረው የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ላይ ሰሞኑን የኢህአዴግ መንግሥት አሳፋሪ ዝቅተኛ ጭማሪ በማድረግ አሹፎብናል ያሉ መምህራን የሁለት ቀን አስቸኳይ የሥራ ማቆም አድማ መቱ፡፡

በአዲስ አበባ ዳርቻዎች የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች እና በመሐል ከተማ የሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ የሁለት ቀን የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለዘጋቢያችን የገለጹ ሲሆን የኢህአዴግ መንግሥት በበኩሉ መምህራን በግዳጅ ገብተው እንዲያስተምሩ በማስፈራራትና በመከፋፈል ላይ ሴራ ላይ እንደሚገኝ ዘጋቢያችን ባደረገው የዳሰሳ ቅኝት አረጋግጧል፡

ዛሬ በአዲስ አበባ የመምህራን የሥራ ማቆም አድማ የተካሄደባቸው አካባቢዎች አቃቂ ቃሊቲ፣ ኮተቤ፣ አስኮ እና አየርጤና ሲሆኑ በመሐል ከተማ ደግሞ ኮልፌ የሚገኘው ሚሊኒየም ሁለተኛ  ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ኮልፌ ኮምፕሬሲፍ ሁለተኛና የመሰናዶ ትምህርት ቤት፣ መርካቶ ጎጃም በረንዳ አካባቢ የሚገኘው አጋዚያን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገኙበታል፡፡

በሁለት ቀን የሥራ ማቆም አድማው ላይ በአቃቂ የሚገኙት በርካታ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ዛሬ የመማር ማስተማር ሂደት ያልቀጠለ ሲሆን በደራርቱ የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤት፣ በገላን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሥራ ማቆም አድማው ተሳታፊ የሆኑ ሥማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ አንድ መምህርና አንዲት መምህርት የሥራ ማቆም እድማ እርምጃው በግብታዊነት የተወሰደ ሳይሆን መብትን ለማስከበርና በየጊዜው የሚንረው የኑሮ ጫና ከቁጥጥራችን ውጪ ወጣ፤ መንግሥት በሚከፍለን ደመወዝ አይደለም አንድ ወር አሥር ቀን መቆየት አልቻልንም፣ የቤት ኪራይ መጨመር፣ የምግብ እህል እጅግ መናር፣ የትራንስፖርትና የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ መናር ከአቅማችን በላይ ሆኖ በችጋር ከማለቃችን በፊት ዛሬ አድማ አድርገናል፣ መንግሥት በአስቸኳይ ጭማሪውን የማያሻሽል ከሆነ አድማው በመላው ከተማ ሁሉ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የኢህአዴግ መንግሥት በበኩሉ ርህሰ መምህራንን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችን፣ እና የኢህአዴግ አባልና ደጋፊ መምህራንን ለአስቸኳይ ስብሰባ እንደጠራ የነገሩን አንድ የፓርቲው አባል መምህር ነገር ግን ይህ የህልውና እና የሰብዓዊ መብት ጥያቄ በመሆኑ ለመገኘት አለመፍቀዱንና በአድማው መቀጠሉን ለዘጋቢያችን አስታውቋል፡፡

ከአምስት ቀን በፊት የአዲስ አበባ መስተዳደር የትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችን በማዛጋጃ ቤት ሰብስቦ መምህራን ምንም ዓይነት የሥራ ማቆም አድማና ተቃውሞ እንዳያደርጉ የአስጠነቀቀ ሲሆን ሁኔታው ወደ ፖለቲካዊ ተቃውሞ ተለውጦ አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ትወድቃለች ብሏል፡፡

ከማዘጋጃ ቤቱ የአዲስ አበባ መስተዳደር የማስፈራራት ስብሰባ በኋላ ውስጥ ውስጡን ለሥራ ማቆም አድማ መምህራን ሲነጋገሩ እንደነበረ መረጃ ደርሶናል ያለ አንድ የፌዴራል ፖሊስ አባል መንግሥት የነገው የሥ ማቆም አድማና የአወሊያ መስኪድ የመጅሊስ ይውረድ ጥያቄ ህዝባዊ ስብሰባ አፈትልኮ ወደ ውጭ እንዳይወጣ ሰግቷል ሲል ለዘጋቢያችን ገልፆል፡፡ 

ኢሳት በቅርቡ የተደረገውን የደሞዝ ጭማሪ የተቃወሙ መምህራን የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ውይይት መጀመራቸው መዘገቡ ይታወሳል

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide