ጥር 28 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል እንዳለው ከምሥራቅ አፍሪካ አልቃይዳ ጋር ጥብቅ ግንኙነት በመመስረት በአገር ውስጥ በማደራጀት፣ ሥልጠናና ትምህርት በመስጠት ሲንቀሳቀሱ የተደረሰባቸው ስምንት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የአልቃይዳ አባላቱ በአገሪቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመታየት ላይ ያለውን የአክራሪነት ዝንባሌ እንደምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ጉዳት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው ብሎአል ግብረሀይሉ።
ተጠርጠሪዎቹ በሶማሊያ አልሸባብና አልቃይዳ፣ በኬንያ፣ በሱዳን፣ በፊሊፒንስ፣ በሳዑዲ ዓረቢያና በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ የአልቃይዳ ህዋሳት ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎአል።
የደህንነቱ ግንረሀይል ያወጣው መግለጫ ገለልተኛ ወገኖችን ሊያሳምን አልቻለም። በአወልያ በሚካሄደው የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ውስጥ አስተባባሪ የሆኑ አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ሰው ለኢሳት እንደተናገሩት፣ መንግስት አልቃይዳ በኢትዮጵያ ውስጥ ህዋስ ሲያደራጅ ደረስኩበት በማለት ያቀረበው ክስ፣ በአወልያና በመላው አገሪቱ ሙስሊሙ ያነሳውን የመብት ጥያቄ ለማፈን ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አገራቸውን ይወዳሉ፣ ያነሱትም የመብት ጥያቄ ነው፣ እንቅስቃሴያችን ከአልቃይዳ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ መንግስት የሙስሊሙን አመራሮች ለማሰርና ጥያቄውን ለማፈን ሰበብ እየፈለገ ነው፤ እኛም በዚህ ተደናግጠን ጥያቄያችንን ከመጠየቅ ወደ ሁዋላ አንልም ብለዋል።
በሌላ በኩል መንግስት ምናልባትም ከአሜሪካ መንግስት ፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ከሂውማን ራይተስ ወች፣ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ከሌሎችም የሰብአዊ መብት ተቋማት የጸረ ሽብር ህጉ የአገር ውስጥ የዲሞክራሲ እንቅስቃሴን ለማፈኛነት እየዋለ ነው የሚለውን ወቀሳ ለማቀዝቀዝ የፈጠረው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል እኝሁ አስተያየት ሰጪ አክለዋል።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ ኢትዮጵያ የፀረ-ሽብር ህጓን ታሻሽላለች የሚል ተስፋ እንዳላቸው የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቢል በርንስ ገለጸዋል
“የኢትዮጵያ የፀረ ሽብር ሕግና አፈጻጸም፤ የመናገር ነፃነትንና ነፃውን ሚዲያ ሊያቀጭጭ ይችላል” በማለት ነው ለራሳቸው ለመለስ ፊት ለፊት የነገሯቸው-የዩናይትድ ስቴትስን የልዑካን ቡድን በመምራት ሰሞኑኑ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ላይ የተሳተፉት የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር በርንስ።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ማለታቸውን የጠቆሙትም፤ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን መጠናቀቅ ተከትሎ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ከተወያዩ በሁዋላ፤ አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሆነው በሰባት አገራት ከሚገኙ ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት የቴሌ ኮንፈረንስ ላይ ነው።
የውጭ ጉሳይ ሚኒስትሩ ከዚህም ባሻገር ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በዲሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ በጥልቀት መወያየታቸውን ተናግረዋል።
በቴሌ ኮንፈረንሱ ላይ የኢትዮጵያ ፀረ ሽብር ሕግ አፈጻጸም የመናገር ነፃነትንና ነፃውን ሚዲያ ሊያቀጭጭ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው የጠቆሙት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቢል በርንስ፤ይህንኑ ስጋታቸውን ከመለስ ጋር በተወያዩበት ወቅት መግለፃቸውን ተናግረዋል።
በኢኮኖሚው ረገድ የአሜሪካ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉባቸው ዕድል እያደገ መምጣቱን መገንዛባቸውን የገለጹት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ይሁንና ከዲሞክራሲ ግንባታ ጋር በተያያዘ የዲሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባት፣ ለሕግ የበላይነት መገዛትና የሰብዓዊ መብትን ማክበር ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ከአቶ መለስ ጋር በስፋት መነጋገራቸውን ነው ያመለከቱት።
የፀረ ሽብር ሕጉን ጉዳይ አንስተው ከአቶ መለስ ጋር በተወያዩበት ወቅት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፦ አሜሪካ ለመናገር ነፃነትና ለነፃ ሚዲያ ያላትን ቁርጠኝነት ለመለስ በግልጽ አስታውቀዋቸዋል፡፡
የመናገር ነፃነትና የነፃ ሚዲያ መኖር ለማንኛውም አገር የዲሞክራሲ ዕድገት ያለውን ጠቀሜታም በዝርዝር ለ አቶ መለስ እንዳስረዷቸው፤ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
“ማንኛውም መንግሥት የሽብር ጥቃትን የመከላከል ግዴታ እንዳለበት ለማንም ግልጽ ነው” ያሉት የአሜሪካ ምክትል የውጩ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር በርንስ፣ ሆኖም ኢትዮጵያ የሽብር ጥቃትን ለመከላከል በሚል በቅርቡ ያፀደቀችው የፀረ ሽብር ሕግ ግን ተግባር ላይ ሲውል የመናገር ነፃነትንና የነፃ ሚዲያውን ሊያቀጭጨው እንደሚችል ያላቸውን ስጋት “ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ገልጬላቸዋለሁ”ብለዋል፡፡
ስለሆነም፤ የፀረ ሽብር ሕጉ በጥንቃቄ ታይቶ እና ተከልሶ የመናገር ነፃነትን በሚያረጋግጥ መንገድ ይሻሻላል የሚል ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ሚስተር በርንስ ተናግረዋል፡፡
በዩናይትድ ስቴትስና በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ግንኙት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥታቸው ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ከዚሁ ጋር ሳይለያይ አገራቸው ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ የምትሰጠውን ድጋፍም አጠናክራ እንደምትቀጥልም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብር ህግ ፤ የመናገርና የመፃፍ መብትን በመንፈግ ህዝቡን ጸጥ አድርጎ ለመግዛት የተዘጋጀ የ አፈና መሳሪያ በመሆኑ በ አስቸኳይ ውድቅ እንዲሆን፤እንዲሁም በዚሁ ህግ መሰረት መንግስት ያሰራቸውን ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች በ አስቸኳይ እንዲፈታ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ የፕሬስ ነፃነት ተሟጋቾችና የተለያዩ መንግስታት እየወተወቱ ይገኛሉ።