ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በ አባይግድብ ዙሪያ በመካከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን ውዝግብ ይፍታል የተባለ ስምምነት መፈራረማቸውን  የግብጹ አህራም ኦንላይን ዘግቧል።

መጋቢት ፲፬(አስራ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሶስቱ ሀገራት የፈረሙት ስምምነት በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት በግድቡ ምክንያት በግብጽና በ ኢትዮጵያ መካከል  የነበረውን ውጥረት የሚያስቀር ነው ብሏል-አህራም።

“የዓባይ ወንዝ ለሺህዎች ዓመታት በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሲፈስ ኑሯል”ብለዋል የግብጹ ፕሬዚዳንት አል ሲ ሲ -ስምምነቱን ለመስማት በካርቱም ለተሰባሰቡ የተፋሰሱ ሀገራት ልኡካን ባደረጉት ንግግር።

አል ሲሲ አክለውም፦”በመተባበር ትልቅ ነገር መፈጸም አለያም ባለመስማማት እርስበርስ መጎዳዳት እንችላለን፤ እኛ ግን  መተባበሩን መርጠናል”ብለዋል።

በግድቡ ውሃ የመያዝ አቅምና በቴክኒካል ጉዳዮች  የሶስቱም ሀገሮች ደህንነት በሚጠበቅበትና ሶስቱም ሀገሮች ተጠቃሚ በሚሆኑበት ስምምነት ላይ መፈራረማቸውንም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው ሀገራቸው የምትሰራው ግድብ ለ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ብቻ የሚውል በመሆኑ ግብጽን ፈጽሞ የማይጎዳ መሆኑን ተናግረዋል።