(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 13/2011)ኢትዮጵያ በ13ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጠኛ በእስር ቤት የማይገኝባት ሀገር መሆኗ ተገለጸ።
የዓለም ዓቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ የቦርድ አባል ካትሊን ካሮል ሰሞኑን በኒዮርክ የተዘጋጀውን ፕሮግራም አስመልክተው እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እስር ቤቶች የታሰረ ጋዜጠኛ የለም።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ የጋዜጠኞችን እስር በቅርበት እየተከታተለ ሪፖርት የሚያቀርበው ሲፒጄ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ አገዛዝ ከአፍሪካ ሁለተኛው የጋዜጠኞች ቀበኛ አገዛዝ መሆኑን በይፋ መግለጹ የሚታወስ ነው።
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ተሟጋች ተቋምም በየጊዜው በሚያወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያውን አገዛዝ የጋዜጠኞ እስር ከበረከተባቸው የዓለማችን አስር መንግስታት አንዱ አድርጎ አስቀምጦት ቆይቷል።
ሰሞኑን በሲፒጄ አዘጋጅነት በዓለም ዙሪያ መስዋዕትነትን የከፈሉ ጋዜጠኞችን ለማክበር በተዘጋጀ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የሲፒጄ የቦርድ አባል ካትሊን ካሮል በኢትዮጵያ የሚታየውን መሻሻል በመግለጽ አንድም ጋዜጠኛ በእስር ላይ እንደሌለ ተናግረዋል።
ይህም በሃገሪቱ የ13 ዓመታት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው እንደሆነ ነው ካትሊን ያስቀመጡት።
ምርጫ 97ትን ተከትሎ የህወሃት አገዛዝ ላለፉት 13 ዓመታት ያለማቋረጥ ጋዜጠኞችን በማሰር አብዛኞቹም በስጋት ሀገር ጥለው እንዲሰደዱ በማድረጉ በከፍተኛ ደረጃ ሲወገዝ ቆይቷል።
ምርጫውን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ የህወሀት አገዛዝ አፋኝ ህጎችን በማውጣት ኢትዮጵያን ለጋዜጠኞች የማትመች ሀገር እንድትሆን አድርጓታል ተብሎ ሲከሰስ ኖሯል።
በኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማህበር ኢነጋማ መረጃ መሰረት ባለፉት 15 ዓመታት ከ100 በላይ ጋዜጠኞች በህወሀት አገዛዝ በደረሰባቸው አፈና ምክንያት ሀገር ጥለው ተሰደዋል።