የኦብነግ ሰራዊት ሀገር ቤት ገባ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 12/2011) የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ሰራዊት ትጥቁን ፈቶ ወደ ሀገር ቤት ገባ።

የኦብነግ ወደ ሰላማዊ ትግል መግባት ለሶማሌ ክልል ህዝብ ታላቅ የምስራች ነው ሲል የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

ትጥቁን ፈቶ ለገባው የኦብነግ ሰራዊትም በጂጂጋ አቀባባል ተደርጎለታል።

በሌላ በኩል በእስር ላይ በሚገኙት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ የተደራጀውና የክልሉን ሰላምና ደህንነት በማናጋት ነዋሪዎች ላይ አደጋ ሲጥል የቆየው ሄጎ የተሰኘው የወጣቶች ስብስብ ሙሉ በሙሉ መዋቅሩ መፍረሱን የሶማሌ ክልል መንግስት አስታውቋል።

የሄጎ አመራሮች ገሚሱ ሀገር ጥለው ሲያመልጡ ገሚሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ታውቋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1984 ጀምሮ ኦጋዴንን ነጻ ለማውጣት በሚል ዓላማ ብረት ያነሳ ግንባር ነው።

ለአርባ ዓመታት በዘለቀው የትጥቅ ትግል ከደርግ ዘመን ጀምሮ ህወሃት ሀገሪቱን ተቆጣጥሮ እስከዘለቀበት ቅርብ ወራት ድረስ ኦብነግ ከሁለት የኢትዮጵያ መንግስታት ጋር ተዋግቷል።

በ2007 እ አ አ በቻይና የማዕድን አውጪ ኩባንያ ላይ የደረሰውንና የ74 ሰዎች ህይወት ያጠፋውን ጥቃት ሃላፊነት ከመውሰድ ባሻገር በመንግስት ወታደሮች ላይ ጉዳት ማድረሱን የሚገልጹ ጥቃቶችን ሲፈጽም መቆየቱን የግንባሩን የትግል ታሪክ የሚያወሱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከህወሀት አገዛዝ ጋር ተደጋጋሚ ሽምግልናዎችን በማድረግ የዘለቀው ኦብነግ ሁለት ከፍተኛ አመራሮቹ ለድርድር ሄደው በህወሃት ደህንነቶች ታፍነው የተወሰዱበት አጋጣሚም ተፍጥሯል።

ግንባሩ በመጨረሻም ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረገ በኋላ በቅርቡ በአስመራ ከኢትዮጵያ የአሁኑ መንግስት ጋር  በተደረገ ድርድር ትጥቁን ፈትቶ በሰላማዊ ትግል ለመሰማራት መስማማቱ የሚታወስ ነው።

በዛሬው ዕለት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ሰራዊት ትጥቁን ፈትቶ ሀገር ቤት መግባቱ ተገልጿል።

በግንባሩ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ እንደተመለከተው ትጥቅ የፈታው ሰራዊቱ ዛሬ ከአስመራ ተነስቶ ጅግጅጋ ከተማ ገብቷል።

የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ደጋፊዎቻቸው አቀባበል እንዳደረጉለትም ጠቅሷል።

የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የሚዲያ አማካሪ አቶ አብዱላሂ ሁሴን ኦብነግ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ትጥቁን ፈትቶ መግባቱን ለኢሳት አረጋግጠዋል።

በኦብነግ የትግል ዘመን በሶማሌ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

በተለይም የኦብነግ ደጋፊ እየተባለ በቀድሞው ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ከፍተኛ ግፍ በሶማሌ ህዝብ ላይ መፈጸሙን መረጃዎች ያመልክታሉ።

የክልሉ ሰላምና ደህንነት ተናግቶ ህዝቡ ለረሃብ እንዲዳረግ ከተፈጥሮ በተጨማሪ ከኦብነግ ጋር በተደረገ ረዥም የትግል ዓመታት ምክንያት መጠነሰፊ ሰብዓዊ ጥፋት መፈጸሙንም በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር የሚገለጽ ነው።

አቶ አብዱላሂ ሁሴን የኦብነግ ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣት ለክልል ህዝቡ የምስራች ነው። መንግስትም በደስታ ተቀብሎታል ይላሉ።

በሶማሌ ክልል የጸጥታና ደህንነት ስጋት ሆኖ የቆየው ሄጎ የተሰኘው የወጣቶች ቡድን ሙሉ በሙሉ መፍረሱንም የሶማሌ ክልል መንግስት አስታውቋል።

የፕሬዝዳንቱ የሚዲያ አማካሪ አቶ አብዱላሂ ሁሴን ለኢሳት እንደገለጹት በቀድሞ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ የተደራጀው የሄጎ ስብስብ ፈርሶ አመራሩ ገሚሱ ሲያዝ ገሚሱ አምልጦ ከሀገር ወጥቷል።

የሶማሌ ክልል አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል የሚሉት አቶ አብዱላሂ ከጂጂጋ ያለወታደር አጀብ መንቀሳቀስ  አይቻልም ነበር፡ ያ ታሪክ ተቀይሯል ይላሉ።

በመንግስታቱ ድርጅት በተለያዩ ቦታዎች ያገለገሉትና በትምህርቱ መስክ ላቅ ያለ ደረጃ የደረሱት አዲሱ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ ዑመር ስልጣን ከያዙ በኋላ የሶማሌ ክልል ሰላምና መረጋጋቱ የተሻለ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው።

አቶ ሙስጠፋ የሶማሌ ክልል የውስጡን ሰላም በማረጋጋት ለኢትዮጵያ የድርሻቸውን ለማበርከት በሙሉ አቅም በመስራት ላይ መሆናቸውን በቅርቡ ለኢሳት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።