ኢሳት (ሰኔ 21 ፥ 2008)
ኢትዮጵያ የጸጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ተመረጠች። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለጸጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባልነት ስትመረጥ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
በንጉሱ እንዲሁም በደርግ የስልጣን ዘመናት ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ም/ቤት ተመርጣ አገልግላለች።
የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ም/ቤት ካሉት 15 አባላት ውስጥ አስሩ በተለዋጭ አባልነት የሚያገለግሉ ሲሆን፣ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው አምስቱ ቋሚ ሃገራት የዩኤስ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታኒያና ሩሲያ መሆናቸውን ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ከተመረጠችበት ተለዋጭ አባልነት የምታገለግለው እኤአ ከጥር 2017 ጀምሮ እስከ 2018 ለሁለት አመታት መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት እኤአ ከ1967 እስከ 1968 እንዲሁም በደርግ ዘመን እኤአ ከ1989 እስከ 1990 በተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ም/ቤት ተለዋጭ አባልነት አገልግላለች።
በአሁኑ ወቅት በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባል ሆነው በማገልገል ላይ ከሚገኙ 10 አገራት ሶስቱ ከአፍሪካ ሲሆኑ፣ እነሱም አንጎላ፣ ግብፅና ሴኔጋል መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።