ኢትዮጵያ የአባይ ግድብን በተመለከተ ግብፅ ባቀረበችው ሃሳብ እንደምትስማማ ተገለጸ

ኢሳት (ነሃሴ 23 ፥ 2008)

በመገንባት ላይ ባለው የአባይ ግድብ ዙሪያ ላለፉት አራት አመታት ሲወዛገቡ የቆዩት ግብፅ፣ ኢትዮጵያና፣ ሱዳን፣ ልዩነቶቻቸን በማጥበብ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነገረ።  በአባይ ግድብ ዙሪያ የሚወዛገቡት ግብፅና ኢትዮጵያ ግብጽ ባቀረበችው የትብብር ሰነድ ላይ  ስምምነታቸውን መግለጻቸውን የግብፅና የሱዳን መገናኛ ብዙሃን የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋቢ በማድረግ ትናንት ዕሁድ ዘግበዋል።

በግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በመርህ ደረጃ የተስማሙበትን ጉዳይ አስመልክቶ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር ዕሁድ ለመገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ፣ ሶስቱም አገሮች በግብፅ የቀረበውን የስምምነት ሰነድ በመቀበላቸው ልዩነቶቻቸው ሙሉ በሙሉ ተፈቷል ሲሉ ተናግረዋል።

የስምምነቱን ሙሉ ዝርዝር የሶስቱ አገሮች መሪዎች ወደፊት በሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እንደሚያደርጉ የተናገሩት ጋንዱር፣ ሆኖም ስምምነቱ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና የጸጥታ ጉዳዮችን  የሚመለከት ነው ተብሏል።

ስምምነቶችን መቀበላቸው ሶስቱ አገራት ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገራቸው እንደሚያሳይ የገለጹት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ በግብጽ የቀረበውን ትብብር ሰነድ በሁሉም ወገን ተቀባይነት ይኖረዋል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።

በድርድሩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡት የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ሶስቱም አገራት ችግሮቻቸውን በመፍታታቸው ከዚህ በኋላ ስምምነቱ እንደማይፈርስ ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት አራት አመታት ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ስለማይኖር ምንም አይነት ማስተካከያ አይደረግበትም ሲል አቋሙን ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል።

ሆኖም ግብጽና ኢትዮጵያ በግድቡ ተጽዕኖው ላይ ስምምነት ሊደርሱ ባለመቻላቸው ሁለት የፈረንሳይ  ኩባንያዎች መምረጣቸውና በዚሁ በገለልተኛ አካል የሚያካሄደው ጥናት ማሻሻያ እንዲያደርግበት ከተፈለገ ማሻሻያውን ተግባራዊ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ መንግስት ለግብፅ  መንግስት የማረጋገጫ ፍንጭ መስጠቱ ይታወሳል።

ይህንኑ ተከትሎ በግድቡ ላይ ማብራሪያን የሰጡት ፕሬዚደንት አል-ሲሲ ሃገራቸው የነበራት ስጋት እየቀነሰ መምጣቱን ለህዝባቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።

ይሁንና የግብፅ አቋም በምን ምክንያት ሊቀየር እንደቻለ ዝርዝር መግለጫን አለመስጠታቸው ታውቋል። ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለማጥናት የተመረጡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያና ግብፅ ከኩባንያዎቹ ጋር በመስከረም ወር ላይ ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ኩባንያዎች ይፋ የሚያደርጉት የጥናት ውጤት ይግባኝ የሌለው እንዲሆን ከዚህ በፊት በካርቱም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።