በአዲስ አበባ መጽሃፍ አዟሪዎች እየታሰሩ ነው ተባለ

ኢሳት (ነሃሴ 23 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች መጽሃፍ በማዞር የሚተዳደሩትን ዜጎች እያሰሩ እንደሚገኙ ተገለጸ። መጽሃፍት አዟሪዎቹ “ኅብረተሰቡን ለአመፅ የሚገፋፉና ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ መጻሕፍት በማዘዋወርና በመሸጥ” በሚል ክስ እንደተወነጀሉ በአገር ውስጥ የሚታተሙ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት መጽሃፍት አዟሪዎች በተለይም በአዲስ አበባ በተለያዩ እርስ ቤቶች ታስረው የሚገኙ ሲሆኑ፣ እስካሁን ድረስ ለተጠረጠሩበት ወንጀል ፍርድ ቤት ያልቀረቡ እንዳሉም ከአገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

አመጽ የሚያነሳሳ መጽሃፍቶችን ትሸጣላችሁ ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉት ቁጥራቸው ያልታወቁ የመጽህፍት አዟሪዎች፣ ፍትህ ጋዜጣ ላይ አመጽ የሚያነሳሳ ጽሁፍ አሳትሟል በሚል የሶስት አመት እስራት የተበየነበት የተመስጌን ደሳለኝ “የፈራ ይመለስ” መጽሃፍ ይዘው በመገኘታቸው እንደሆነ ከሃገር ቤት የደረሰን መረጃ የመለክታል። ከዚህ በተጨማሪ ከሳምንታት በፊት የአማራ እና የኦሮሞ የዘር ግንድን የሚመለከት መጽሃፍ የጻፉት የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሃፍ የያዙ አዟሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።  የጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው መጽሃፍ፣ “የዘመኑ ጥፋት” የሚል መጽሃፍ የያዙ መጽሃፍት አዟሪዎችም በአገዛዙ ፖሊሶች መታሰራቸው ታውቋል።

መጽሃፍቱ አመጽ ቀስቃሽ በመሆናቸው፣ አዟሪዎችም ከጸሃፊዎች ጋር ተባባሪ ስለሆኑ በወንጀል እንደሚጠየቁ ፖሊስ መግለጹን በአገር ውስጥ የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

የመጽሃፍ አዟሪዎች ስራ “በድብቅ የሚሠራ ሕገወጥ ተግባር” መሆኑን የገለጸው ፖሊስ፣ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር የዋሉ መጽሃፍት አዟሪዎችን ፍርድ ቤት ለማቅረብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ማስፈለጉን ገልጿል።

ሆኖም የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ብሄረሰብንና ህዝብን የሚያዋርድ መጽሃፍ እንዲሸጥ በሚያበረታታበት አገር ህዝብን ከህዝብ የሚያቀራርብ መጽሃፍት ህዝቡ እንዳያነባቸው መከልከሉ ከፍተኛ የአገዛዙር ዘረኝነት የሚያሳይ መሆኑ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

ኢሳት ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች የኢትዮጵያን አንድነት መጽሃፍት ግጭት ይቀሰቅሳል መባሉ ግልጽ እንዳልሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“የታተመ መጽሃፍ ወንጀል ሊሆን ይችላል ወይ? ብለው የጠየቁት ሌሎች የድረገጽ ተጠቃሚዎች፣ መጽሃፍት አዟሪዎች መጽሃፉን ሸጠው ትርፍ ከማግኘት ውጪ መጽሃፍቶችን ለማንበባቸውም እርግጠኛ አይደለንም  ሲሉ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ሃሳባቸውን አስፍረዋል።