መጋቢት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ድርጅቱ አመታዊውን የውሃ ቀን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በሚሊኒየም የልማት ግቦች የተቀመጠውን ለ62 በመቶ የሚሆነው ህዝብ እስከሚቀጥለው አመት የንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የማድረጉን እቅድ ተሳካለች።
ይሁን እንጅ ይላል ድርጅቱ ህዝቡ ንጹህ መጸዳጃዎችን እንዲያገኝ በማድረግ በኩል አገሪቱ በእጅጉ ወደ ሁዋላ ቀርታለች። የሚሊኒየም የልማት ግቡ 51 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ንጹፍ መጸዳጃ እንዲያገኝ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ አገሪቱ ማሳካት የቻለችው 8 በመቶውን ብቻ ነው። በትምህርት ቤቶች ውስጥም 33 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት ብቻ ንጹህ የመጸዳጃ አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን፣ 31 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ብቻ የነጹህ ውሃ ተጠቃሚ ናቸው።
በንጹህ ውሃ አጠቃቀም በኩል በገጠርና በከተማ መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩም በሪፖርቱ ተመልክቷል። በዩኒሰፍ ሪፖርት መሰረት 43 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አሁንም ንጹህ የመጠጥ ውሃ አያገኙም።
በቻይና 108 ሚሊዮን፣ በህንድ 99 ሚሊዮን፣ በናኢጀሪያ፣ 63 ሚሊዮን፣ በኢትዮጵያነ 43፣ በእንዶነዢያ፣ 39 ሚሊዮን፣ በኮንጎ 37 ሚሊዮን፣ በባክንግላዲሽ 26 ሚሊዮን ፣በታንዛኒያ 22 ሚሊዮን፣ በኬንያ 16 ሚሊዮንና በፓኪስታን 16 ሚሊዮን ህዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ አይደለም። ዩኒሴፍ አብዛኞቹን መረጃዎች የሚያገኘው ከኢትዮጵያ መንግስት ነው።