ነሃሴ ፰(ስምንት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አሜሪካ በሰጠችው የአጎዋ የገበያ ዕድል ቀነ ቀጠሮ ማራዘም ላይ በሰፊው ሲመክር የነበረው 12ኛው የአጎዋ ጉባዔ አፍሪካ ዕድሉ እንዲራዘም መፈለጓን የአሜሪካ የህግ አውጭ ምክርቤት ተወካዮች ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቁላቸው በመጠየቅ ተጠናቋል፡፡
በ12ኛው የአጎዋ ፎረም የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ኢትዮጵያ ባለፉት 12 ዓመታት ወደ አሜሪካ የላከችው ምርት በየዓመቱ በአማካይ 80 በመቶ ጭማሪ ያሳዬ ቢሆንም፤ ከወጪ ምርቱ የተገኘው ገቢ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር በጣም በአነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአሜሪካ መንግሥት በአጎዋ በኩል ለአህጉሪቱ የሰጠው ዕድል ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥ ለማምጣትና ትርጉም ያለው እድገት ለማስመዝገብ ያለው አስተዋዕኦ የጎላ መሆኑን አቶ ኃይለማርያም ተናግረዋል። ይሁንና አፍሪካውያኑ ዕድሉ ለመጠቀም በቂ ምርት የማቅረብ እጥረት ስላለባቸው ዕድሉን በሚፈለገው መጠን ሳይጠቀሙ እንደቀሩ ተናግረዋል። አጎዋ የአፍሪካና የአሜሪካ ዋነኛ የኢኮኖሚና የንግድ የትብብር ማዕከል በመሆኑ አፍሪካውያኑ ይህን ክፍተት በማስወገድና ችግሩን በመገንዘብ እድሉን መጠቀም ይኖርባቸዋል።
የኢትዮጵያን ችግር በርካታ አፍሪካውያን አገራት እንደሚጋሩት ገልጸው፣ የአጎዋን እድል ለመጠቀም አፍሪካውን የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል። አፍሪካውያን የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ያለውን የንግድ እድል በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ እያገኙ በመምጣታቸው የረዥም ጊዜ እቅድ ማዘጋጀት ጀምረዋል።
አህጉሪቱ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትና ሽግግር ለማድረግ የአጎዋ እድል በ2015 ይጠናቀቃል፡፡ ቢያንስ ለቀጣዮቹ ከ15-20 ዓመታት ሊራዘም እንደሚገባ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የአሜሪካ የንግድ ተወካይ አምባሳደር ማይክል ፍሮማን በበኩላቸው አፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ስኬት እንደሚመዘገብበት ቀጣዩ አህጉር እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል። አሜሪካ በአፍሪካ አህጉር በቀጣይ የሚኖረው ኢኮኖሚ ስኬት ዋነኛ አጋር ሆና የመቀጠል ጽኑ ፍላጎት ያላት እንዳላት ፕሬዚዳንት ኦባማ መግለጻቸውንም ተናግረዋል።
ከጉባዔው መጠናቀቅ በፊት የህክምና መድሐኒቶች በአጎዋ የገበያ ዕድል ውስጥ እንዲካተቱ፣ የንግድ ዕድሎችና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ለማስፋፋት የሚያስችል የፋይናንስ ምንጭ እንዴት ማግኘት ይቻላል በሚሉት እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ በዝግ ስብሰባዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ እንደገለጹት መድሐኒቶችንና የህክምና መሳሪያዎችን በማምረት በአጎዋ የገበያ ዕድል ለማቅረብ መልካም ፍላጎት በአሜሪካውያኑ ተወካዮች በኩል መታየቱን በመግለጽ፣ ውሳኔው የአፍሪካውያንን ፍላጎት ያማከለ እንዲሆን ተወካዮች እንደሚሰሩ የገለጹላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመዝጊያ ስነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በቅርቡ አፍሪካን በመጎብኘት ለአፍሪካ ህዳሴ እውን መሆን ያላቸውን ጥረት በማውሳት የአጎዋ የገበያ ዕድል መራዘምንም በተመለከተ የአሜሪካን ህግ አውጭ ምክር ቤት አባላትን ወክለው የተገኙት ልዑካን የአፍሪካን ፍላጎት ለምክር ቤቱ በመግለጽ እንደሚራዘም ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡
ላለፉት 12 ዓመታት አገራቸው ለተመረጡ 39 የአፍሪካ አገሮች በሰጠችው የኮታና የታሪፍ ነፃ ገበያ ዕድል፣ እ.ኤ.አ. በ2000 ከነበረው ስምንት ቢሊዮን ዶላር፣ በ2012 ወደ 35 ቢሊዮን ዶላር በማደግ አፍሪካውያንን የጠቀመ የገበያ ዕድል መፈጠሩን አውስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአጎዋ ዕድልን ባገኘችበት ወቅት ታገኝ ከነበረው ይልቅ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደቻለች ሲናገሩም፣ በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ600 ሺሕ ወደ 1.6 ሚሊዮን ዶላር ያደገ ገቢ የሚያስገኙ ምርቶችን ወደ አሜሪካ መላክ እንደቻለች ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአጎዋ ገበያ የምታሳየው ዕድገት ከእንፉቅቅ እንደመነሳት ሲሆን፣ በአሜሪካ ኩባንያዎች ፍላጎት ላይ የተመረኮዘ የጥራት፣ የብዛትና በተባለው ጊዜ ምርትን የማስረከብ ችግሮች በኢትዮጵያ ላኪዎች ዘንድ ጎልተው የሚታዩ ችግሮች እንደሆኑም አምባሳደር ቡዝ ተናግረዋል፡፡
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2001 ጀምሮ የአጎዋ ፎረም በየዓመቱ በአሜሪካና የአጎአ ተጠቃሚ በሆኑ የአፍሪካ አገራተ ሲካሄድ ቆይቷል።