ኢትዮጵያ ከአምናዋ ሻምፒዮን ዛምቢያ ጋር ተመደበች

ጥቅምት ፲፬ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመጪው ጥር በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው የ29ኛው እግር ኳስ ዋንጫ የምድብ ድልድል ወጥቷል፤ ኢትዮጵያ በምድብ ሶስት፤ ከአምናዋ ቻምፒዮን ዛምቢያ፤ ቡርኪናፋሶና ናይጄሪያ ጋር ተደልድላለች።

ዛሬ፤ ረቡእ ጥቅምት 14 ቀን በደቡብ አፍሪካዋ ከተማ ደርባን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማና የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት፤ ኢሳ አያቱ በተገኙበት ስነስርአት በወጣው እጣ፤ ኢትዮጵያ ከሶስቱ አገሮች ጋር ተደልድላለች።
ደቡብ አፍሪካ በምድብ አንድ ከአንጎላ፤ ሞሮኮና ካሜሩንን አሸንፋ እዚህ የደረሰችውና ለመጀመሪያ ግዜ በአፍሪካ ዋንጫ የምትሳተፈው ኬፕ ቨርዴ ጋር ስትወጣ፤ በምድብ ሁለት ደግሞ ጋና፤ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ፤ ኒጀርና ማሊ ወጥተዋል።
በምድብ አራት አይቮሪኮስት፤ ቶጎ፤ አልጀሪያና ቱኒዚያ ተመድበዋል። ግብጽ በዚህ ዙር የአፍሪካ ዋንጫ አትሳተፍም።
በሌላ ዜና፤ ሁለት ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋቾችና አንድ አለማቀፍ ዳኛ የኢትዮጵያ ቡድን ባገኘው ድል የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። የቀድሞው የብሄራዊ ቡድኑ ግብ ጠባቂ ተካበ ዘውዴ፤ የመሀል አጥቂው ሙሉጌታ ወልደየስና የእግር ኳስ ተጫዋችና አለማቀፍ ዳኛው ግርማ ታፈሰ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፤ ቡድኑ ከአመታት በሁዋላ ለድል
በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ከሶስቱም ታዋቂ ሰዎች ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለምልልስ በኢሳት ቴሌቪዥንና ሬድዮ በመጪው ቅዳሜና እሁድ እናቀርባለን።
29ኛው የአፍሪካ የእግር ኳስ ዋንጫ ከቅዳሜ ጥር 11 እስከ እሁድ የካቲት 3 (ጃንዋሪ 19 እስከ ፌብሩዋሪ 10) በደቡብ ይካሄዳል። ኢሳት ውድድሩን እየተከታተል ከቀድሞ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ጋር በታጀበ ትንታኔ እንደሚያቀርብ ከወዲሁ ያስታውቃል።