(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 14 /2010)
የዓለም የኢኮኖሚክስ ፎርም የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ባለፉት ስድስት ወራት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ1.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝቻለሁ በማለት ያወጣውን የውሸት ሪፖርት ውድቅ አደርገው።
ፎርሙ ከዘርፉ የተገኘው 440 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ብሏል።
በሌላ በኩል ወደተለያዩ አካባቢዎች የተጓዙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ጉዟቸው መስተጓጎሉንና በመከላከያ ሰራዊት አጃቢነት ወደ ሐዋሳና አርባምንጭ ተወስደው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውንና ሌሎችም ጉዟቸውን እየሰረዙ መሆናቸውም ታወቋል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ከግዜ ወደግዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን የዘርፉ ባለሙያዎችና የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይናግራሉ።
እነዚህ አካላት እንደሚሉት የቱሪዝም እንቀስቃሴው ለመዳከሙ በዋናነት የሚጠቀሰው በሀገሪቷ ውስጥ ያለው አለመርጋጋት መሆኑንም ያነሳሉ ።
በተለይም ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በሀገሪቷ ተከስቶ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞና እንቢተኝነት የውጭ ሃገር ጎብኚዎች ወደ ሀገሪቱ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ መሰረዝ አሊያም የግዜ ቆይታቸውን በማሳጣር ወደ መጡበት ሲመለሱ ተስተውለዋል ።
ይህ በሆነበት ታዲያ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የቱሪዝም ዘረፉ ውጤታማ መሆኑንና አለም አቀፍ ጎብኝዎችም ወደ ሀገሪቱ ያለስጋት እየገቡ ናቸው። ከፍተኛ ገቢም አገኝቻለሁ በማለት መግለጫ መስጠቱን ቀጥሏል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት 1.8 ቢሊዮን ዶላር ወይም 54 ቢሊዮን ብር ከዘርፉ ማግኘቱን ሪፖርት አድርጓል ።
ይሁንና የዓለማቀፉ የኢኮኖሚክስ ፎረም ይህንን ቁጥር የውሸት ነው በማለት ውድቅ አድርጎታል።
እንደ ፎረሙ ከሆነ ገቢው 444 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ13 ቢሊዮን 320 ብር በታች ነው።
የኢኮኖሚክስ ፎረሙ ይህንን የገቢ መጠን ሲጠቅስ ጎብኚዎቹ በሀገሪቱ የሚቆዩበት ግዜን መሰረት በማድረግ መሆኑንም ተናግሯል ።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ቱሪስቶች በሀገሪቱ ከ5 እስከ 7 ቀናት ይቆያሉ በማለት በሪፖርቱ አካቷል።
የዓለማቀፉ ተቋም ግን አብዛኛው ጎብኚ ለስብሰባና ለስራ የሚመጣ በመሆኑ ይህንን ያህል ጊዜ ሊቆዩ አይችሉም ቆዩ ቢባል እንኳን ከ2 እስክ 3 ቀናት ብቻ ነው በማለት አሃዙ ተቀባይነት የለውም ሲል ውድቅ ማድረጉን መረዳት ተችሏል።
በተያያዘ ዜና ወደ ኦሮሚያ ክልል እና ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ለጉብኝት የተጓዙ ጎብኚዎች በኦሮሚያ በአካባቢው ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ ሳቢያ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ተገልጿል።
ጎብኚዎቹ በመከላከያ ሰራዊት አጃቢነት ወደ ሐዋሳና አርባ ምንጭ ተወስደው ወደ አዲስ አባባ መመለሳቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ የአስጎብኚዎች ማህበር ፕሬዝዳንትን አቶ ያዕቆብ መላኩን በመጥቀስ ዘገቧል።
ከ45 በላይ የሚሆኑት እነዚሁ ጎብኚዎች ባሌ ጎባ፣ዝዋይና ሻሸመኔ አካባቢ የነበሩ መሆናቸውም ታወቋል።
በኦሮሚያ አካባቢ ባለው ህዝባዊ እንቢተኝነት ሳቢያ በርካታ መንገዶች በመዘጋታቸው ጎብኚዎች መንገዶች እስኪከፈቱ ለመጠበቅ መገደዳቸውና ሌሎችም ጉዟቸውን በመሰረዝ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ታወቋል።
በሌላ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ እቅድ የነበራቸው ጉብኚዎችም ጉዟቸውን መሰራዛቸውም ተነግሯል።