(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 12/2011)የሱዳን እና የኢትዮጵያ መንግሥታት እስረኞችንና የተያዙ ንብረቶችን ተለዋወጡ፡፡
በቅርቡም በወሰን አካባቢ አልፎ አልፎ የሚነሱ ግጭቶችን ማስቆም በሚቻልባቸው እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተው የሁለቱም ሀገራት ኢታማዦር ሹሞች በተገኙበት ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡
በኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት የ33ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ዓለሙ በሱዳን ታስረው የነበሩ ስድስት ኢትዮጵያውያን፣ ሁለት የእርሻ ትራክተሮች፣ አንድ ሞተር ሳይክል እና ከ40 ሺህ ብር በላይ ለኢትዮጵያ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ በኩልም ታስሮ የነበረ አንድ ግለሰብ፣ ሁለት የእርሻ ትራክተሮች እና አንድ ላንድ ክሮዘር መኪና ለሱዳን ተመልሷል ነው ያሉት፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል ዓለሙ እንደገለጹት አልፎ አልፎ በሁለቱም ሀገራት አዋሳኝ ቦታዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች አሉ።
እናም ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታትም የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች በመከባበርና በሰላም እንዲኖሩ በጋራ እና በተናጠል እየተሠራ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ጉዳዮች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የተጀመረው የእስረኞችና የንብረት ርክክብ ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ያነሱት ብርጋዴር ጄኔራሉ ወደፊት የተሻለ የፀጥታ ሥራ እንደሚሠራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የሱዳን መንግሥትም የቀሩና ያልተፈቱ ችግሮች ካሉ ለማስተካከል ዝግጁ መሆኑን ማስታወቁን መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡