መጋቢት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መቀሌ/ ወልድያ፣ ሰመራ ታጁራ የሚባለውን የባቡር ሃዲድ ፕሮጀክት ግንባታን ለመስራት ኢትዮጵያ 34 ቢሊዮን ብር የሚሆን ገንዘብ የመደበች ሲሆን ፣ መስመሩ አሰብን ለማለፍ ሲባል ተጨማሪ 6 ቢሊዮን ብር ወይም 300 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስወጣት ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል። አገሪቱ ይህን ያክል ገንዘብ ለመክፈል የተገደደችው ባበሩ የሚያልፍበትን የተወሰነ የአሰብ አካባቢ ሳይነካ ለማሳለፍ በመገደዱዋ ነው።
ይህ የባቡር ግንባታ በተለይም በዳሎል አካባቢ የሚገኘውን ፖታሽ ወደ ውጭ ለማጓጓዝ ታስቦ የሚሰራ ነው። ፕሮጀክቱን የቱርክ ኩባንያ የሆነው ያፒ መርከዚ ኮንትራት ወስዶ በ42 ወራት ውስጥ ይሰራዋል። ለፕሮጀክቱ ግንባታ አገሪቱ ብድር በማፈላለግ ላይ ስትሆን እስካሁን ቻይና እና አንድ የስዊዘርላንድ ባንክ ብድር ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡