(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 28/2010) ኢትዮጵያ ክፋት በተሞላበት የፖለቲካ ችግር ምክንያት አሁንም መስቀለኛ መንገድ ላይ እንደምትገኝ የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።
የ2010ን የበጎ ሰው ልዩ ሽልማትን ሲቀበሉ አቶ ለማ መገርሳ እንደገለጹት ጥፋትን የሚያስከትለው የክፋት ፖለቲካ እንዲቀር ሁሉም መተባበር ይኖርበታል።
አቶ ለማ መገርሳ የበጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ የሆኑት በተለያዩ ዘርፎች ተሸላሚ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን መካከል ነው።
የበጎ ሰው ሽልማት ያገኙት ኢትዮጵያውያን በምርጥ መምህርነት፣በጋዜጠኝነት እንዲሁም በልዩ ልዩ ስራዎች የተመረጡ ናቸው።
በሽልማት ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በኢትዮጵያ ክፋትና ሸር የተሞላበት ፖለቲካ የብዙ ኢትዮጵያውያንን በልቷል ሲሉ ተናግረዋል።
በመጠፋፋት መኖር እርግማን ነው ያሉት አቶ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያ አሁንም መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ለማ መገርሳ ገለጻ ኢትዮጵያ ቆሻሻ የፖለቲካ ታሪኳን አራግፋ ወደ ጥሩ የፖለቲካ ባህል መሸጋገር ይኖርባታል።
እናም የጥፋት ፖለቲካ እንዲቀርና ሁሉም እንዲተባበር አቶ ለማ ጥሪ አቅርበዋል።
በአሁኑ ጊዜ ተስፋና ሰጪ የሆኑና አስቸጋሪ የሚባሉ ነገሮች እንዳሉ ነው የገለጹት አቶ ለማ መገርሳ።
በኢትዮጵያ በለውጡ ሂደት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የልዩ የበጎ ሰው ሽልማት ቢደረግላቸውም ለኔ ይገባኛል ብዬ አላምንም።እኔ ለሃገሬ ያበረከትኩት አስተዋጽኦ አነስተኛ ነው ሲሉ ገልጸዋል።