አክቲቪስት ታማኝ በየነ ባህርዳር ገባ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 28/2010) በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ትላንት ደማቅ አቀባበል የተደረገለት አክቲቪስት ታማኝ በየነ ዛሬ ባህርዳር መግባቱ ታወቀ።

ነገ ደግሞ ወደ ጎንደር እንደሚያቀና የተገለጸው ታማኝ በየነ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም ቀጣይ መርሃ ግብሮች ተዘጋጅተውለታል።

በብሔራዊ ቲያትር እንዲሁም በሚሊኒየም አዳራሽና በባህርዳር ስታዲየም እንደትላንቱ ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን እየሰበከ የቀጠለው ታማኝ በየነ ቅዳሜ ማለዳ አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ብሔራዊ ቲያትር ቤት በከፍተኛ አጀብ የተጓዘው አክቲቪስት ታማኝ በየነ በአንጋፋና ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎች በብሔራዊ ቲያትር ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

አብራው ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘችው ባለቤቱ አርቲስት ፋንትሽ በቀለም በሱ ምክንያት ከሙያዋ ጭምር በመለየት የከፈለችውን መስዋዕትነትነት አስታውሷል።

ታማኝ በየነ ወደ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን በመሄድም በአንጋፋዎቹ አርቲስቶች ጥላሁን ገሰሰና ታምራት ሞላ እንዲሁም በወጣቱ አርቲስት ታምራት ደስታ መካነ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን አስቀምጧል።

በዚህ ዕለት ቀትር ላይ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር የተገናኘው አክቲቪስት ታማኝ በየነ ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋርም በኢዮቤልዩ ቤተመንግስት መምከሩ ታውቋል።

እሁድ ከቀትር በኋላ ከ25 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት እጅግ ደማቅ ስነስርአት በሚሊኒየም አዳራሽ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት አክቲቪስት ታማኝ በየነ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አማካኝነት የእንኳን ደህና መጣህ መልዕክት ተላልፎለታል።

ኢንጂነር ታከለ ኡማም ለሰብአዊ መብት መከበርና በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በዚህ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው ደማቅ ዝግጅት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳና የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

ዛሬ ባህርዳር ሲገባ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት አክቲቪስት ታማኝ በየነ በባህርዳር ስታዲየም ቁጥሩ ከፍተኛ ለሆነው ታዳሚ በከፍተኛ ድጋፍ የታጀበ ንግግር አድርጓል።

በአማራነታችሁ 27 አመታት የደረሰባችሁን ግፍና ሰቆቃ ብገነዘምብ መዳኛው ግን ኢትዮጵያውያነት ነው ሲል መልዕክት አስተላልፏል።

ጋምቤላዎች በአንድ ቀን ከ400 በላይ ተጨፍጭፈዋል።

ሶማሌዎች በአየር ተደብድበዋል በደሉ ሁሉም ላይ ተፈጽሟል ያለው ታማኝ በየነ እንደትላንቱ ሁሉ “ዛሬም የኦሮሞ ደም የእኔ ደም ነው”እያላችሁ ኢትዮጵያዊነታችሁን አሳዩ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ከትግራይ ውስጥ የወጡ ጥቂት ጨካኞችና ግፈኞች በፈጸሙት ድርጊት የትግራይ ሕዝብ ተጠያቂ ስላልሆነ ከትግራይ ሕዝብ ጋር በጋራ በኢትዮጵያዊነት እንቁም ሲል ጥሪ አቅርቧል።

የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ብናልፍ አንዱአለም ለአክቲቪስት ታማኝ ምስጋና አቅርበዋል።