ኢትዮጵያ ሃኪሞቿንና ሰራዊቷን ወደ ምእራብ አፍሪካ ለመላክ መወሰኑዋ አነጋጋሪ ሆኗል

ጥቅምት ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንን እህቶቻችን ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ ኢትዮጽያዊን የህክምና ባለሙያዎችን ከመከላከያ ሰራዊትና ከሌሎችም ተቋማት በሸታው ወደተስፋፋባቸው የምዕራብ አፍሪካ

ሀገራት ለመላክ መወሰኑን አረጋግጠዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት «ኢትዮጽያ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዋ ሀገር እንደመሆንዋ መጠን አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ለማገዝ የራሳችን ድርሻ መወጣት አለብን የሚል አቋም ተይዟል፡፡ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ

ያሉና ሌሎችም የጤና ሙያተኞች በፈቃደኝነት እንዲሳተፉ ዓለም አቀፍ ትብብር ማድረግ እንደሚገባን ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡በከፍተኛ ጥንቃቄ በአፍሪካ የራሳችን ሚና ልንጫወት ይገባል ብለዋል፡፡»ሆኖም የበሽታው ስርጭት አሳሳቢ በሆነበትና ከኢትዮጽያም የተሻሉ ሀገራት

ጥንቃቄ ላይ ባተኮሩበት በዚህ ወቅት የኢትዮጽያ መሪዎች በቁጥር እጅግ አነስተኛ የሆኑ የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎችን ወደምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ተቻኩለው ለመስደድ የወሰኑበት አግባብ በርካታ ኢትዮጽያዊንን ግራ አግብቶአል፡፡በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሐኪሞችና የነርሶች

እጥረት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ በገጠር እየተገነቡ ያሉ ጤና ጣቢያዎች ያለባለሙ ባዶዋቸውን መሆናቸው እየታወቀ ለተራ ዝና ሲባል ጥቂት ባለሙያዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲሰሩ መወስኑ ተገቢ አለመሆኑን አስተያየት የጠየቅናቸው የጤና ባለሙዎች ተናግረዋል፡፡

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጦሩዋን ውደ ምእራብ አፍሪካ እንድትልክ በቅርቡ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር በተገናኙበት ወቅት ጥያቄ ሳይቀርብላቸው አልቀረም። ፕሬዚዳንት ኦባማ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት

ያሞካሹት ይህንን ጥያቄ ለማቅረብ ሊሆን ይችላል ብለው ይገምታሉ። በተያያዘ ዜና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር  ዶክተር ዲላሚኒ ዙማ የአፍሪካ ሀገራት የኢቦላ በሽታ ሥርጭትን ለመግታት በጎ ፈቃደኛ የህክምና ባለሙያዎችን በመላክ ድጋፍ እንዲያደርጉ በትላንትናው

ዕለት ይፋዊ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ታማሚዎች የሚታከሙባቸው የጤና ተቋማት፣ የመሰረት ልማትና የህክምና ባለሙያዎች እጥረት ማጋጠሙን የጠቀሱት ሊቀመንበርዋ ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ የምዕራብ አገራት

ትብብር በማድረግ ላይ መሆናቸው አመልክተዋል። በአንፃሩ በበሽታውና በቫይረሱ ሥርጭት በስፋት በተጠቁት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ያጋጠመውን የህክምና ባለሙያዎች እጥረት ለመሙላት የኅብረቱ አባል አገራት የህክምና ባለሙዎችን በመላክ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

በሽታው በስፋት በሚስተዋልባቸው ላይቤሪያ፣ ጊኒና ሴራሊዮን እስከሁን ያሉት የበጎ ፈቃደኛ የህክምና ሙያተኞች ቁጥር ከ100 እንደማይበልጥ ጠቅሰው የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር ለአፍሪካ አገሮች የትብብር እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2014 የኢቦላ ቫይረስ በምዕራብ አፍሪካ ከተከሰተ ወዲህ 4 ሺህ 997 ሰዎች የሞቱ ሲሆን  9 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በሰባት ሀገራት በበሽታው የተያዙ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።