ኢትዮጵያ፡ ለስኳር ልማት ሲባል አርብቶ አደሮች መሬታቸውን በግዳጅ እንዲለቁ እየተደረገ ነው

ሰኔ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በቂ ምክክር ሳያደርግ ወይም ተገቢውን የካሣ ክፍያ ሳይፈጽም በመንግስት የሚካሄድ የስኳር ልማትን ለማስፋፋት የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያ የታችኛው የኦሞ ሸለቆ ነዋሪ የሆኑ አርብቶ አደሮችን በግዳጅ እያፈናቀለ ነው ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ ባወጣው ሪፖርት ገለጸ።  ሪፖርቱ ከዚህ በፊት ያልታተሙ እና የመስኖ መስመሮችን፣ የስኳር ማምረቻ ፋብሪካዎችን እንዲሁም ሌሎች ለንግድ የሚውሉ ሰብሎችን ለማማረት የሚውል 100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ሄክታር ጨምሮ በኦሞ ሸለቆ ለማካሄድ የታቀደውን ሰፊ ልማት የሚያሳዩ የመንግስት ካርታዎችን ያካተተ ነው።

 

ሰማንያ አምስት ገጾች ያሉትና “ ‘ረሃብ ቢመጣ ምን ሊኮን ነው?’፡ በኢትዮጵያ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ተወላጅ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸሙ በደሎች” በሚል ርዕስ የወጣው ይኸው ሪፖርት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሃይልና ማስፈራራትን በመጠቀም ነዋሪዎቹን ከጥንት ጀምሮ ከኖሩበት መሬት እንዴት እንዲለቁ እንደሚያደርጓቸውና ይህም የነዋሪዎቹን ሁለንተናዊ የኑሮ ሁኔታ ያለ ምንም የካሣ ክፍያና አማራጭ የኑሮ መሠረት በማስቀረት እንዴት አደጋ ላይ እንደጣለው የሚዘረዝር ነው።  የመንግስት ባለስልጣናት በልማት ዕቅዱ ላይ ጥያቄ ባነሱ እና ተቃውሞአቸውን በገለጹ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ነዋሪዎች ላይ የዘፈቀደ እስር፣ድብደባና ሌሎች የሃይል እርምጃዎችን ወስደዋል።

“ኢትዮጵያ በኦሞ ሸለቆ ለማካሄድ ያሰበችው ሰፊ የልማት ዕቅድ በዚያ የሚኖሩ ዜጎችን መብቶች ከግምት ውስጥ ያስገባ አይመስልም ፣” ያሉት በሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ከፍተኛ ተመራማሪ ቤን ራውለንስ፣ “ልማት አቋራጭ መንገድ የለውም፤ በዚያ የሚገኘውን መሬት ለዘመናት የኑሮ መሠረታቸው አድርገው የኖሩ ሕዝቦች ሃሳባቸውን ሊጠየቁና ካሣ ሊከፈላቸው ይገባል።” ብለዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች በሰኔ 2003 ዓ.ም. ከ 35 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎችና ከ 10 የእርዳታ ሰጪ ሀገራት ተወካዮች ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረገ ሲሆን ከዚያ ጊዜ በኋላም ቢያንስ 30 ሌሎች እማኞችን አነጋግሮአል። ሂዩማን ራይትስ ዎች አካባቢውን በጎበኘበት ወቅት ነዋሪዎችን ለማስፈራራትና ከስኳር ልማቱ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ተቃውሞዎችን ለማፈን የጦር ሠራዊት አባላት በመንደሮቹ በየጊዜው ቅኝት ያደርጉ ነበር። ወታደሮቹም (የመንደርተኞቹን) ከብቶች ይሰርቃሉ ወይም ይገድላሉ።

 

“ምን ልበላ ነው?” ይላሉ የሙርሲ ብሔረሰብ አባል የሆኑ አንድ ሰው ለሂዩማን ራይትስ ዎች ሲናገሩ። “ከብቶቼን በሙሉ ወስጄ እንድሸጥና አንድ ብቻ ከቤቴ እንዳስቀር ነገሩኝ። አንዱን ከብት ምን ላደርገው ነው? እኔ ሙርሲ ነኝ። ረሃብ ቢመጣ የላም አንገት ወግቼ ደም እጠጣለሁ። ከብቶቹን ሁሉ ለገንዘብ ከሸጥናቸው እንዴት ነው የምንበላው?”  ሂዩማን ራይትስ ዎች አካባቢውን ከጎበኘ በኋላ ያሰባሰባቸው ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት የክልሉ ባለስልጣናት እና የጸጥታ ሃይሎች ባላፈው ዓመት የስኳር ልማቱን ለማካሄድ በሚከለለው ቦታ እያረሱ ይኖሩ ከነበሩ የአካባቢው ተወላጆች መሬት በሃይል ነጥቀው ወስደዋል። ነዋሪዎች በሃይል መፈናቀላቸውን እና የመሬት ምንጣሮ መካሄዱን የሚያመላከቱ ሪፖርቶችም እየበረከቱ መጥተዋል።

የኦሞ ወንዝን ውሃ ማግኘት በሸለቆው ውስጥ ለሚኖሩት አርብቶ አደሮች የምግብ ዋስትና እና የኑሮ ዘይቤ እጅግ አስፈላጊ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የከብቶቻቸውን ቁጥር መቀነስ እና በአንድ አካባቢ መስፈር እንዳለባቸው እንዲሁም በኦሞ ወንዝ

ያላቸው ተጠቃሚነትም እንደሚቀር የክልሉ ባለስልጣናት ያለምንም ተጨማሪ ውይይት ገልጸውላቸዋል።__

ዕቅዱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ በኦሞ ሸለቆ የሚኖሩ ቢያንስ 200,000 ሰዎችን እንዲሁም ድንበር ተሻግሮ በሚገኘውና 90

በመቶ የሚደርሰውን ውሃውን ከኦሞ ወንዝ በሚያገኘው በቱርካና ሐይቅ አካባቢ የሚኖሩ ሌሎች 300,000 ኬንያውያንን ሕይወት

የሚነካ ነው። የጊቤ ሦስት ግድብ እና በመስኖ የሚካሄደው የንግድ ግብርና የሚያስከትሉትን ጥምር ተጽዕኖ የሚፈትሽ አዲስ የአካባቢ

እና የማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲካሄድ ኬንያ ግፊት ማድረግ አለባት ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች።

 

በርካታ ዓለማቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የጊቤ ሦስት የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊ እና

የአካባቢ ተጽዕኖ በማንሳት ስጋታቸውን የገለጹ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ ባሳየው ግልጽነት የጎደለው አካሄድና ነፃ የሆነ

ግምገማ ባለማድረጉ ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል።ምክንያቱን በይፋ ባይገልጽም የኢትዮጵያ መንግስት የዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት

ባንክ የጊቤ ግድብ ፕሮጀክትን በገንዘብ እንዲደግፉ አቅርቦ የነበረውን ጥያቄ አንስቷል።የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴም ፕሮጀክቱ

በቱርካና ሐይቅ ላይ የሚያስከትለውን ውጤት አስመልክቶ ተጨማሪ ነፃ የሆነ ግምገማ እስኪደረግ ድረስ ፕሮጀክቱ እንዲቆም ሀሳብ

አቅርቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት የበጀቱን ከፍተኛ ድርሻ የሚያሟላው ከዓለማቀፍ ለጋሾች በሚያገኘው ዕርዳታ ነው። የጸጥታ ሃይሎች እና በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ የወረዳ አስተዳደር ባለስልጣናት ደመወዝም ከዚሁ ፕሮግራም በሚገኝ ገንዘብ የሚከፈል ነው። ለፒቢኤስ ፕሮግራም ትልቁን የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉትም ብሪታንያ፣የአውሮፓ ህብረት፣ኔዘርላንድስ እና ጀርመን ናቸው።

የልማት እንቅስቃሴዎቹ ከሀገሪቱ ሕጎችና ከዓለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች መርሆች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ መካሄድ እስኪችሉ ድረስ

የኢትዮጵያ መንግስት የጊቤ ሦስትን ግንባታ እና ተያይዞ የሚካሄደውን የስኳር ልማት እርሻ እንዲያቆም ሂዩማን ራይትስ ዎች ጥሪውን

አቅርቧል። በደቡብ ኦሞ ተጨማሪ ኢንዱስትሪያዊ የልማት ሥራ ከማካሄዱ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት የኦሞ ሸለቆ ተወላጅ

ማህበረሰቦች ለዘመናት በኖሩበት መሬታቸው ላይ ያሏቸውን መብቶች ማክበር፣መሬታቸው ለምን አገልግሎት ሊውል እንደታሰበ እና

የካሣ ክፍያን አስመልክቶ ትርጉም ያለው ውይይት ከነዋሪዎቹ ጋር ማድረግ አለበት። ለጋሾችም የሚሰጡት ገንዘብ በግዳጅ ለማፈናቀል

ወይም የተወላጅ ማህበረሰቦችን መሬት በሕገ ወጥ መንገድ ለመውረስ እየዋለ እንዳልሆነ ማረጋገጥ አለባቸው ብሏል ሂዩማን ራይትስ

ዎች።

“ኢትዮጵያ የተፋጠነ የኢኮኖሚ ልማትን ለማምጣት ያላት ፍላጎት የሚደገፍ ነው፤ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሞ ሸለቆ እየታየ

ያለው ሁኔታ በአካባቢው ተወላጅ ማህበረሰቦች መብቶች እና በኑሮ መሠረታቸው ላይ ተቀባይነት የሌለው ጫና እያሳደረ ነው፣” ያሉት

ራውለንስ “መንግስት ተፈላጊዎቹን መመዘኛዎች እስኪያሟላ ድረስ ሂደቱን ማቆም አለበት፤ለጋሾችም የሚሰጡት ዕርዳታ የሚፈጸሙትን

በደሎች እያገዘ እንዳልሆነ ማረጋገጥ አለባቸው።” በማለት አክለዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide