የካቲት ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያ ፋሺስት ጣሊያንን ድባቅ የመታችበት የአድዋ ድል 120ኛ አመት በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጭ በሚኖሩ ዜጎች ተከብሯል።
የአድዋን ድል በማስመልከት አርበኞች ግንቦት7 ባወጣው መግለጫ ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያን ለመውረርና ህዝቧን በውርድትና በባርነት ለመግዛት የዘመተብንን የጣሊያንን ጦር አለምን ማስደነቅ ብቻ ሳይሆን የታሪክን አቅጣጫ ቀይሯል ብሎአል።አድዋ ሲነሳ ልንረሳው የማንችለው ነገር “በግር በፈረስ ከሀገራችን ልዩ ልዩ ቦታዎች የብሔረሰብም ሆነ ሌላ ልዩነት ሳያግዳቸው እንደ አንድ ሰው የተነሱ አባቶቻችንን የህብረት ተጋድሏቸውን ነው” ያለው አርበኞች ግንቦት7፣ ተዋርዶና ተንበርክኮ መገዛትን ምንም ያህል ቢጠሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ባይነሱ ይህን አንጸባራቂ ድል ይቀዳጁ ነበር ብሎ ማሰብ ይከብዳል” ብሎአል።
መግለጫው አክሎም ” ሀገራችንን የወረሩ ጠላቶች ሁሉ ሊጠቀሙበት ሞክረው ያልቻሉትን የከፋፍለህ ግዛ ሴራ በመጠቀም እንደባዕድ ሊገዛን እየሞከረ ያለውና ሀገራችንን ካላንዳች ይሉኝታ በመዝረፍና ልጆቹዋን ካለርሕራሔ በመጨፍጨፍ ላይ የሚገኘውን የሁላችንም ጠላት የሆነውን ወያኔን ከላያችን ላይ አሽቀንጥረን የምንጥለውና ነጻነታችንን የምንቀዳጀው እንደ አድዋው ጊዜ አብረን የተነሳን እንደሆን ብቻ ነው”ይላል።”ወያኔ 25 ዓምት የፈነጨብንና ሀገራችንን ከባዕድ ባልተናነሰ ዛራፊነትና ጨፍጫፊነት ሊገዛ የቻለው የውበታችን ምልክት የሆነውን ብሔረሰባዊ ልዩነታችንን እየተጠቀመ ይሁን እንጂ ብዙዎቻችንም ተመሳሳይ ዓላማ ይዘን በህብረት ለመታገል ባለመወሰናችን ካባቶቻችን ያድዋ ትሪክ ባለመማራችን መሆኑን መካድ ” እንደማይቻልም ገልጿል።
የአድዋን ድል ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ሰፊ ትንተና የሚያደርገው የንቅናቄው መግለጫ፣ ” ዛሬ በኦሮሚያ ምድር የህዝቡን መሬት ካለይሉኝታ የሚዘርፈው ወያኔ፣ ሕጻን ሽማግሌ ሳይለይ መደዳውን ኦሮሞ ወገኖቻችንን የሚጨፈጭፈው ወያኔ ፣ ድንበር ቆርሶ ለመስጠት ከጀርባችን ሆኖ የሚደራደረው የተባበረና ወያኔ፣ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ማንነቴን ከናንተ ይበልጥ የማውቀው ራሴ ነኝ ስላላቸው እየነቀሱ የሚያፍኑትና ይስንቱን ቤት ለዘላለሙ እንዲዘጋ ያደረገው ወያኔ፣ ይህን ሁሉ የሚፈጽመው ” የሚተባበር ሕዝብ የለም በሚል ተስፋ ነው” ነው ብሎአል።
ንቅናቄው፣ ለመከፋፈላችን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን ብሎአል።
መግለጫው በመጨረሻም “ወገኖቻችን በገፍ አየተጨፈጨፉ መፈጠራቸውን ሊጠሉ በቻሉበት ደረጃ ደርሰዋል፤ በየቦታው አመጾች በመቀጣጠል ላይ ናቸው፤ ወያኔ በተወሰነ ደረጃ የህዝቡ ቁጣ ስላስደነገጠው የሚያውቀውን የመጨፍጨፍና የመቀጥቀጥ ፖለቲካ በስፋት ተያይዞታል ስለዚህ ” አድዋ ላይ ጠላትን ተባብረው እንዳንበረከኩት አባቶቻችን፣ ራሳቸውንና እኛን ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን መላውን ጥቁር ህዝብ እንዳኮሩትና የአለም ታሪክን አቅጣጫ እንደቀየሩት ሁሉ እኛም ተባብረን እንነሳ። እንደ አድዋው አባቶቻችን እንሁን።” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
በአድዋ ድል ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶች በማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃን በተለይም በፌስቡክ እየተሰጡ ነው። አጃሜ የተባለ ጸሃፊ “አድዋ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር ነጭን ድል ያደረገበት ጦርነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ በአውሮፓውያን ቅኝ አገዛዝ ስር ያልወደቀች የጥቁሮች ምድር እንድትባል ምክንያት የሆነም ጭምር፡፡ ፍፁም የሆነ የሀገር ፍቅርና ጠንካራ አንድነት ከሰለጠነ ወታደራዊ ሀይል እንደሚሻል የታየበት፣ ለሌሎች ጥቁር ህዝቦች ትግል መነሳሳት ምክንያት የሆነ የውጊያ አውድማ ነው አድዋ፡፡” ብሎአል።
ዳዊት አስራደ በዛብህ “የአድዋን ድል ባሰብኩ ጊዜ ” ከሚያመኝ ህመሜም የምፈወስበት ጊዜ እንደቀረበ ይሰማኛል።ጎበዝ ለከርሞ በጀግንነትና በኩራት፡ በሽለላና በፉከራ፡ በአባቶቸ ክብር ሆኜ የምንጎማለል ይመስለኛል። የሻገተው የማንነቴን ዶሴ ገልጨ አይቸዋለሁና ለዘንድሮ ወኔ ቢያንሰኝም ለከርሞ በክብር የአባቶቸን ድል በልጃቸው ድል ደግፌ እንደማከብር ይታየኛል።” ብሎአል።
አሌክስ አብርሃ በበኩሉ”ከ120 ዓመት በፊት ነፃነት ተሰጥቶናል,,,,እስካሁን ግን አልተቀበልንም!!” ብሎአል።
አንዋር አንዋር ደግሞ ” አንዲት ኢትዮጵያ በአንድ ንጉስ በማትመራበት ወቅት፣ ስለ አንዲት ኢትዮጵያ ሲሉ በአንድነት የዘመቱት 80,000 ኢትዮጵያዊያን ለዛሬቱ ኢትዮጵያ መገኘት መሰረት ናቸው። ይህ የአድዋ ድል ለኛ ኢትየጵያኖች ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነፃነት ፈር ቀዳጅ ነው፣ ለኛ ኢትዮጵያኖች ደግሞ ኩራታችንም ነው፣ በዘር በሃይማኖት በክልል ሳይመራረጡ በአንድ ሃይል፣ በአንድነት በመነሳት በጦር መሳሪያ ብዛት እና ጥራት በምንም የማይወዳደሩትን ወራሪ፣ በጀግንነትና ለውጭ ወራሪ ጥላቻ ባላቸው ስሜት ተነሳስተው ገጥመው፣ ወራሪውን ድል በመንሳት አሳፍረው በማባረር ከቅኝ ተገዢነት አድነውናል። በመሪነት ከነበሩት አፄ ሚኒሊክ/ እቴጌይቱ ጀምሮ አብረዋቸው ለዘመቱት 80ሺ ዘማቾች በሙሉ በዚህ ድላቸው ክብር አለን፣ ልናመሰግናቸውም ግድ ይለናል።” ሲል ስሜቱን አጋርቷል።
አቤነዘር ቢ ይስሃቅ በበኩሉ “ኢህአዴግ በየአቅጣጫው በተቃውሞ ሲወጠር የአድዋ በዓልን አጥብቆ ለማክበር ሞከረ ፣ ያው ጥላቸው አይለቀውምና የአጼ ሚኒሊክን ሚና ለማሳነስና እሳቸውንም ገለል ለማድረግ ሲታገል ነበር።” ብሎአል።