የገዢው መንግስት አመራሮች ህብረተሰቡ የጦር መሳሪያ ግዥውን እንዲያቆም እየተማጸኑ ነው፡፡

የካቲት ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአማራ ክልል አመራሮች በክልሉ ጠረፋማ ከተሞች በመዘዋወር ህብረተሰቡ አጠናክሮ የያዘውን የመሳሪያ ግዥ እንዲያቆም ሲማጸኑ ተሰምተዋል፡፡
ወጣቱ አመቱን ሙሉ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር የቀን ስራ በመስራትና ከእርሻ የሚያገኙትን ገቢ በቀጥታ ለጦር መሳሪያ ግዥ ማዋላቸው የገዢውን መንግስት አመራሮችን አሳስቧቸዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በመፋፋም ላይ ባለው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በዜጎችና በመንግስት መካከል በሚታየው ፊት መዟዟር የህብረተሰቡን የልብ ትርታ ለማዳመጥ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት የመንግስት አመራሮች፤የጦር መሳርያ በእያንዳንዱ ወጣት እጅ መገኘቱ ለአመጽ ያነሳሳል በሚል ስጋት ላይ መሆናቸው የሚደረሱን የድምጽ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የገዥው መንግስት በጠረፋማ ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶች የጦር መሳሪያ እንዳይገዙ ለማስቆም የወሰነበትን ምክንያት የሚናገሩት አመራር ‹‹ወረዳዎች ጠረፋማ ከመሆናቸው ባሻገር ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚዋሰኑ በመሆኑ ጸረህዝቦች እና ተቀናቃኝ ኃይሎች ለፖለቲካ ትርፍ የሚጠቀሙባቸው አካባቢዎች በመሆኑ ነው፡፡››በሚል እንቅስቃሴው የጸጥታ ችግር ስጋት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የየአካባቢው አመራሮች በቅርበት በመሆን የህብረተሰቡን የልብ ትርታ ማዳመጥ ስላለባቸው በየጊዜው መምጣታቸውንና ህዝቡ በምን አቋም ላይ እንዳለ በመረዳት የሚከሰቱ ችግሮችን ባስቸኳይ ለመግታት እንዲያግዛቸው መሆኑን የሚናገሩት አመራር‹‹ በተለይ ወጣቱ ገንዘቡን ማዋል ያለበት ለወደፊቱ የሚጠቅመውን ለእርሻ ስራ የሚገለገልበትን እንደበሬ ያለ ንብረት መግዛት እንጅ የጦር መሳሪያ አያስፈልገውም፡፡›› በማለት ወጣቱ እየተጓዘበት ያለው መንገድ ትክክለኛ አለመሆኑን ለማስገንዘብ ጥረት ሲያደርጉ ተሰምተዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በጠረፋማ ከተሞችና አካባቢዎች ከፍተኛ የመሳሪያ ሽያጭና ግዥ ግብይትን አሰራር መቆጣጠር ያልቻሉት አመራሮች ነዋሪዎችን በማግባባት በድርጊቱ ላይ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶችን እንዲመክሩ መማጸናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹የአዞእንባ›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡
በተመሳሳይ ዜና ገዢው መንግስት በአማራ ክልል የሚገኘውን የጦርመሳሪያ ለመሰብሰብ ከፍተኛ ፍተሻና አሰሳ በማድረግ ላይ መሆኑን የጸጥታ ዘርፍ ሰዎች ተናግረዋል።
‹‹በየጊዜው መሳሪያ አምጣ በማለት ሰው እናስራለን፡፡›› የሚሉት አመራር ይህ የተደረገበት ምክንያት አሁንም ሆነ በቀጣይ መሳሪያ መያዝ ያለበት ራሱን መጠበቅ የሚፈልግ ሰው ሁሉ ሳይሆን በየአካባቢው የሚነሱ ህዝባዊ አመጾችንም ሆነ እንቅስቃሴዎች ከመንግስት ጋር በመሆን ለማብረድ የሚችል ሰው ነው ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት መሳሪያ የሚገዙትና የታጠቁት ለጸረ ህዝቦች ና ተቃዋሚዎች ክንድ ለመሆን የመንግስትን የመልካም አስተዳደር ጉዞ ለማስተጓጎል የሚጥሩ ወጣቶች መሆናቸውንና እነዚህ ወጣቶች ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው ህይወት የማይጠነቀቁ በመሆናቸው ክትትል በማድረግ መሳሪያ ማስፈታቱን ሊቀጥሉበት ማሰባቸውን ገልጸዋል፡፡
አመራሩ አክለውም ‹‹ በጠረፍ ከተሞች ያሉ አርሶአደሮች ራሳቸውን መምራት የሚችሉ፣ጥሩ አንደበት ያላቸውና ተቻችለው የሚኖሩ በመሆኑ መሳሪያ አያስፈልጋቸውም ወደሚል መደምደሚያ በመደረሱ በቀጣይም አሰሳውና ፍተሻው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡›› ብለዋል፡፡