ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ከሌሎች እስራዔላውያን በበለጠ በወንጀል ድርጊት መጠርጠራቸው ትክክል ነው ሲሉ የእስራኤል ፖሊስ ኮሚሽነር ተናገሩ

ኢሳት (ነሃሴ 26 ፥ 2008)

የእስራዔል መንግስት ፖሊስ ኮሚሽነር የኢትዮጵያ ዝርያ ያላቸው አይሁድ-ኢትዮጵያውያን ከሌሎች አይሁዶች በበለጠ በወንጀል መጠርጠራቸው ትክክል ነው ብለው መናገራቸው ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ። ፖሊስ አዛዡ አይሁድ ኢትዮጵያውያን በወንጀል ድርጊት መጠርጠራቸው ትክክል መሆኑን የተናገሩት በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተጋብዘው በተናገሩበት ወቅት ነው።

የእስራዔል ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ሮኒ አልሼይች በእስራዔል በሚኖሩ አይሁድ ኢትዮጵያውያን ላይ በምን ምክንያት የእስራዔል ፖሊስ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝና፣ በአይሁድ ኢትዮጵያውያን ላይ የዘረኝነት ተግባር ለምን እንደሚፈጸምባቸው ሲጠየቁ፣ “አይሁድ-ኢትዮጵያውያን፣ የእስራዔል አይሁዶች ናቸው፣ ሆኖም በአለም አቀፍ ደረጃ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፣ አዲስ የፈለሱ ሰዎች ከሌላው በበለጠ በወንጀል ድርጊት የሚሳተፉ ናቸው” ሲሉ ለተሰብሳቢው መልሰዋል።

በወንጀል ድርጊት ላይ የተደረጉ አለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት አዳዲስ መጢዎች ያለምንም ጥርጥር በወንጀል ድርጊት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ነው፣ ይህ ደግሞ ሊያስገርም አይገባም፣” በማለት  የፖሊስ ኮሚሽነሩ ሚስተር አልሼይች ባለፈው ማክሰኞ መናገራቸው በስብሰባ ለታደሙ ሰዎች መናገራቸው ታውቋል።

በእስራዔል አገር የሚኖሩ ከ130ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን አይሁዶችን የሚወክሉ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በበኩላቸው፣ ፖሊስ ኮሚሽነሩ ከስራቸው እንዲባረሩ ጠይቀዋል። ባለፈው አመት በሺዎቹ የሚቆጠሩ አይሁድ ኢትዮጵያውያን፣ ባለፈው አመት የእስራዔል ፖሊሶች ኢትዮጵያዊውን ወታደር ሲደበድቡ የሚያሳይ ቪዲዮ ፌስቡክን በመሳሰሉ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ከተለቀቀ በኋላ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የእስራዔል መንግስት እስካሁን ድረስ በፖሊስ አዛዡ ላይ የወሰደው እርምጃ እንደሌለም ለማወቅ ተችሏል።