በኮንሶ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራ ማቆማቸው ተነገረ

ኢሳት (ነሃሴ 26 ፥ 2008)

የደቡብ ክልል የብሄረሰቦች ምክር ቤት ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓም የኮንሶ ህዝብ የራስ አስተዳደር ጥያቄ ውድቅ መደረጉን የሚግልጽ ደብዳቤ መጻፉን ተከትሎ፣  በወረዳዋ የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ስራ ማቆማቸው ተነገረ።

የኮንሶ ህዝብ ከ50 ሺ በላይ ፊርማ አሰባስቦ/ ባለበት ልዩ ወረዳ ሆነው እንዲቀጥሉ አለዚያም ወደ አንድ ራሱን የቻለ ዞን እንዲያድጉ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣  የክልሉ መንግስት የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የኮንሶ ልዩ ወረዳ ወደ ሰገን ዞን እንዲጠቃለል ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።

የደቡቡ ክልል ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ ወር  በጻፈው ደብዳቤ  “አጠቃላይ የጥያቄው ይዘትና ምክንያቶችን መርምሮ በማየት የኮንሶ ህዝብ መሰረታዊና ቀጥተኛ ጥቅሞችንና ሌሎች ህገመንግስታዊ አላማዎችን ለማሳካት እንዲቻል ህዝቡ አሁን ባለበት በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን እንዲቀጥልና  ለብቻው በዞን ለመደራጀት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት የለውም” ሲል ገልጿል።

ይህ ውሳኔ የደረሳቸው የኮንሶ ነዋሪዎች፣ በጉዳዩ ላይ ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ሲመክሩ እንደነበር የገለጹት ምንጮች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመንግስት መስሪያ ሰራተኞች፣ የጤና ጣቢያ ሰራተኞችን ጨምሮ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሰራተኞች ሙሉ በሙሉ ስራቸውን ከማቋረጣቸው በተጨማሪ፣ ሰራተኞቹም የመንግስት ደሞዝ እስካሁን እንዳልወሰዱ ለማወቅ ተችሏል። የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሰራተኞችና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሰራተኞች በስራ ገበታቸው ላይ እንዳልተገኙም የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ትንናንት ረቡዕ ዘግቧል።

ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ፣ በኮንሶ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደግጭት ሊያመራ እንደሚችልና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊዳርግ እንደሚችል የኮንሶ ነዋሪዎች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት የመንግስት ሰራተኞች ስራ አቁመው ደሞዝ ሲከፈላቸው ቢቆይም ፣ አሁን ግን የመንግስት ሰራተኞችና የአገልግሎት ሰጪ ሰራተኞች የመንግስትን ደሞዝ አለመውሰዳቸው ታውቋል።

በኮንሶ ወረዳ ከአስተዳደራዊ ጥያቄ ጋር በተነሳው ተቃውሞ ለእስር ከተዳረጉ ነዋሪዎች በተጨማሪ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።