የካቲት 16 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቃሊቲ እስር ቤት የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆነውን አንዱአለም አራጌን በመደብደብ ጉዳት ያደረሰው የእድሜ ልክ ፍርደኛው ኢብሳ አስፋው ፣ አንዱአለም ኦሮሞነቴን ጠቅሶ ስለሰደበኝ ነው የደበደብኩት በማለት የኦሮሞ ተወላጅ እስረኞችን ለማነሳሳት ሙከራ አድርጎ እንዳልተሳካለት የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ለኢሳት ገልጠዋል።
ኢብሳ አንዱአለምን ከደበደበ በሁዋላ ሌላው የአንድነት የአመራር አባል ወደ ሆነው አቶ ናትናኤል መኮንን ክፍል ተዛውሮ ከናትናኤል ጎን እንዲተኛ ተደርጓል።
እስረኞች “አንዱአለምን ለምን መታከው?” ብለው ሲጠይቁት “ዘሬን ጠቅሶ ስለሰደበኝ ነው”፣ በማለት ሲመልስ ፣ የኦሮሞ ተወላጆች የአንድነት አመራር አባላት ጸረ-ኦሮሞ በመሆናቸው የማስተካከያ እርምጃ ያስፈልጋቸዋል ብሎ በይፋ ሲቀሰቅስ ተሰምቷል።
አንዱአለምን የተረፉትና አብረውት የታሰሩት ሰዎች የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ኦልባና ሊሌሳ ሆነው እያለ እንዴት አንዱአለምን በዘረኝነት ትከሳለህ፣ አንዱአለምና አቶ ኦልባናስ ጓደኞች አይደሉም ወይ? ተብሎ ሲጠየቅ የሚመልሰው አልነበረውም።
በእስር ላይ የሚገኙት የአንድነት አመራር አባላት የኢብሳን ተልእኮ በመረዳት ከሌሎች የኦሮሞ ተወላጆች ጋር በጋራ በመሆን የእስር ቤቱ ባለስልጣናት አማራውን ከኦሮሞው ለማጋጨት የሸረቡት ሴራ ነው እያሉ ለሌሎች እስረኞች ሲያስረዱ ሳምንቱን ማሳለፋቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
የእስር ቤቱ ባለስልጣናት የሸረቡት ሴራ እጅግ አደገኛ ነበር ያሉት ምንጫችን፣ በመጀመሪያ የኦሮሞ ተወላጆችን አንዱአለም ኦሮሞን ስለሚጠላ ነው የተደበደበው የሚል ወሬ እንዲነገር ካደረጉ በሁዋላ፣ ቅስቀሳውን ኢብሳ በራሱ አንደበት እንዲናገረው ፈቅደውለታል ተብሎአል።
ይሁን እንጅ የሌሎች ክልል እስረኞች አንዱአለምን ያተረፈው የኦህኮ አመራር አባል መሆኑን በመገናኛ ብዙሀን ቀደም ብለው ሰምተው ስለነበር፣ የእስር ቤት ባለስልጣናት የሸረቡት ተንኮል መሆኑን ደርሰውበታል።
ኢብሳ ያካሄደው ቅስቀሳ ቢሰራ ኖሮ በናትናኤል ላይ ብቻ ሳይሆን በአማራና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል ከፍተኛ ግጭት ይነሳ እንደነበር ምንጫችን አክለዋል።
እስረኞቹ አሁን ያሉበት ሁኔታ ለደህንነታቸው አስተማማኝ አለመሆኑንም ለማወቅ ተችሎአል። በአብዛኞቹ እስረኞች ላይ ከፍተኛ የሞራል ጥንካሬ ይታያል ተብሎአል።
በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ አካላዊ ጉስቁልና ቢታይበትም፣መንፈሱ ግን አሁንም ጠንካራ ነው። እስክንድር መንግስት በፕሮፓጋንዳ ብዛት እውነትን ለመሸፈን የሚያደርገው ሙከራ እንደሚያበሳጨው ለማወቅ ተችሎአል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide