ጥር 28 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢ ኤም ኤፍ ድረገጽ ስራአስኪያጅ የሆነው ዳዊት ከበደ እንደዘገበው በአትላንታ በተዘጋጀው ታላቅ ምሽት ላይ ቁጥሩ በብዙ መቶ የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ ተገኝቶ ነበር። ገና ከጅምሩ በዚህ ዝግጅት ላይ አርቲስት ታማኝ በየነ፣ አርቲስት ሻምበል በላይነህ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እና ልጅ ተክሌ በክብር እንግድነት ተገኘተዋል።
አርቲስት ታማኝ በየነ፣ አርቲስት ሻምበል በላይነህ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እና ተክለሚካኤል አበበ በእንግድነት የተገኙበትን ይህን ዝግጅት ልዩ የሚያደርገው ኢትዮጵያዊያን በዝግጅቱ ላይ እንዳይገኙ በኢህአዴግ ወኪሎች ማስፈራሪያ ሲካሄድ መቆየቱ ነው።
“ኢሳት በአሸባሪነት የተፈረጀ ድርጅት በመሆኑ፤ ይህ ድርጅት በሚያደርገው ማናቸውም ዝግጅት ላይ የሚገኙ ሁሉ አሸባሪዎችን በመደገፍ ወንጀል የሚጠየቁ ይሆናሉ፤ “በስፍራው ተገኝተን ፎቶ እና ቪዲዮ በማንሳት ማንነታችሁን እናጋልጣለን” በማለት አዲሱ የኢህአዴግ በኩር ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነውና ቅንድቡ በሚለው ለመለስ ዜናዊ በተጫወተው ዜማ የሚታወቀው ሶሎሞን ተካልኝ ሲናገር እንደነበር ዳዊት አስታውሷል።
በዝግጅቱ ላይ የክርስትና እና የእስልምና አባቶች ንግግር ማድረጋቸውም ተዘግቧል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ሪቪው የሚዲያ ሚና ለዲሞክራሲ ለውጥ በሚል የተለያዩ ጋዜጠኞችን በመጋበዝ በዋሽንግተን ዲሲ ዝግጅት አቅርቧል።