ነሀሴ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኢምሬት አንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ባለፈው ማክሰኞ የተነሳ የእሳት ቃጠሎ የስድስት ሰዎች ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ከነኚህም አንደኛዋ ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛ መሆኗን “ዘ-ናሽናል” የተሰኘው ድረ ገጽ ዘገበ።
“አጅማን” ከተማ አቅራቢያ “አል-ሃሚድያ” የተሰኘ አካባቢ በሚገኝ ቪላ ውስጥ በድንገት ቤታቸው ውስጥ እሳት መነሳቱን ያዩት እናት፣ አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግላቸው የስልክ ጥሪ ያደርጋሉ። ሆኖም በደቂቃዎች ልዩነት ከእሳቱ ይወጣ በነበረው ከፍተኛ ጭስና ንዳድ የተነሳ፣ የ7፣ የ11 እና የ14 ዓመት እድሜ ያላቸው ሴት ልጆቻቸው፣ እንዲሁም የኢንዶኔዥያና የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው ሁለት የቤት ሰራተኞቻቸውን ጨምሮ እርሳቸውም ሲሞቱ፣ የ15 ዓመት ዕድሜ ያለው ልጃቸው ግን በመስኮት ዘሎ ሕይወቱን ማትረፉ ታውቋል።
የእሳት አደጋ ማጥፊያው ግብረ ሃይል፣ የስልክ ጥሪው በተደረገ በስድስት ደቂቃዎች ውስጥ ከስፍራው እንደደረሰ የገለፁት የአካባቢው ፖሊስ ባለስልጣን፣ የእናትዬውና የሁለቱን የቤት ሰራተኞቻቸው አስከሬን የምድር ቤቱ ወለል ላይ፣ የሶስት ሴት ልጆቻቸው በድን አካል ደግሞ መኝታ ቤት ውስጥ እንደተገኘ አስረድተዋል።
የአደጋው መንስዔ የምርመራው ውጤት እንዳለቀ እንደሚገለጽ የተናገሩት እኚሁ ባለስልጣን፣ እሳቱ የተነሳው ከኤሌክትሪክ ጋር በተያያዘ ችግር መሆኑን ግን አስታውቀዋል። በአደጋው ህይወቷ የተቀጠፈው ኢትዮጵያዊ ስምና ማንነት ለጊዜው ማወቅ አልተቻለም።
በተያያዘ ዜና ባሳለፍነው ወር ዱባይ ላይ የምትሰራበት ቤት ውስጥ በተነሳው እሳት ጉዳት የደረሰባት አዜብ አበበ፣ ባለፈው ሳምንት ሃሙስ ከዚህ አለም በሞት መለየቷን ይኸው ድረ ገጽ ዘግቧል።
የ24 ዓመቷ ወጣት አዜብ፣ ከማለዳው 12 ሰዓት ከሩብ አካባቢ ለአሰሪዎቿ ቁርስ ለመስራት ደፋ ቀና ስትል፣ በደንብ ባለመገጠሙ ይተነፍስ የነበረ የጋዝ ሲሊንደር ፈንድቶ በተቀጣጠለው እሳት፣ 80 በመቶ የሚሆነው የሰውነት ክፍሏ በአስከፊ ሁኔታ የተለበለበ ሲሆን፤ በዚህም የተነሳ ዱባይ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ተኝታ በህክምና ስትረዳ ቆይታለች። ሆኖም የደረሰባት ጉዳት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ሃኪሞች ሕይወቷን ለመታደግ ያደረጉት ጥረት ከ18 ቀናት በላይ ሊዘልቅ ሳይችል ቀርቶ፣ በአሳዛኝ ሁኔታ ማረፏ ታውቋል።
ሟች ወጣት አዜብ፦ የ4 ዓመት ሕፃን ልጇን፣ እንዲሁም አቅመ ደካማ እናት አባቷን በምታገኘው ገንዘብ ታስተዳድር እንደነበር የጠቀሰው አሰሪዋ፣ በዚህም የተነሳ ቤተሰቦቿን በቀጥታ መርዳት የሚቻልበት መንገድ እንዲያመቻቹለት ዱባይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ካውንስለር ማነጋገሩን አስታውቋል። ሟቿ ህይወቷ ከማለፉ ከአንድ ቀን በፊት በተኛችበት ሆስፒታል ተገኝተው እንደ ጠየቋት የገለፁት ካውንስለሩም፣ ኦማን ለምትገኘው እህቷ የተፈጠረውን ነገር እንደሰማች አስታውቀው፤ አገር ቤት የሚገኙት ወላጆቿም ይኸው አሳዛኝ መርዶ በቅርቡ ይነገራቸዋል ብለዋል።
የሕንድ ዜግነት ያለው አሰሪዋ መሱድ ሰላም፣ ለ9 ወራት ያህል በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ያገለገለቻቸው ሟች አዜብ አበበ፣ ታማኝ፣ ትጉህና ታታሪ በመሆኗ በቤተሰባቸው ዘንድ እጅግ ተወዳጅ እንደነበረች ገልጾ፣ በድንገት በደረሰባት አደጋ በእጅጉ በማዘናቸው እርሱም ሆነ ቤተሰቡ ሕይወቷን ለመታደግ የተቻላቸውን ጥረት እንዳደረጉ ይናገራል። የህክምና ወጪዋም ከቤተሰቡ አቅም በላይ እየሆነ በመጣበት ወቅትም፣ በፌስ ቡክ ላይ ከበጎ አድራጊዎች፣ እንዲሁም በሙስሊሞች የጾም መፍቻ ሰዓት ላይ የተዋጣ 70 ሺህ የዱባይ ገንዘብ ማሰባሰብ እንደቻለ አስታውቋል። ይህም ገንዘብ ሟቿ ኢንሹራንስ ስላልነበራት የህክምና ወጪዋን ለመሸፈን እንደሚውልም ለዜና ድርጅቱ ገልጿል።
መሱድ ሰላም የሟቿን አስከሬን ወደ አገር ቤት ለመላክ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመክፈል የተስማማ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ካውንስለር ግን ግለሰቡ ለሟቿ ቤተሰቦች ጉዳት ካሳ የሚከፍልበትንም መንገድ እየተነጋገሩ መሆኑን ይኸው የዜና ዘገባ ያስረዳል።
በመጨረሻም፦ ኩዌት ውስጥ አህመዲ በተባለ አካባቢ የምትኖር አንዲት ኢትዮጵያዊ፣ ከምትሰራበት ቤት ከሚገኘው መታጠቢያ ክፍል ውስጥ ጽንስ ስታስወርድ መገኘቷን አረብ ታይምስ የተሰኘው ድረ ገጽ ትናንት ዘግቧል።
እንደዚሁ ዘገባ ከሆነ፦ ድንገት ቤታቸው ውስጥ ከፍተኛ ጩኸት የሰሙት የቤቱ ባለቤቶች፤ ድምጹን ወደሰሙበት ክፍል ሲያመሩ፣ ኢትዮጵያዊቷ ሰራተኛቸው በሆዷ ደብቃ ይዛው የነበረውን ጽንስ ስታስወርድ ደርሰውባታል። በሁኔታው የተደናገጡት የልጅቷ አሰሪዎችም ባስቸኳይ ወደ ሕክምና ጣቢያ በመውሰድ በሃኪሞች እርዳታ ጽንሱ ሙሉ ለሙሉ እንደወጣላት ታውቋል። በኩዌት ጽንስ ማስወረድ ሕገ ወጥ በመሆኑ፣ ፖሊስ የጽንሱን አባት ለማወቅና ቀጣይ ምርመራ ለማድረግ፣ የልጅቷን ጤንነት መመለስ እየጠበቀ መሆኑ ታውቋል ሲል ቅዱስ ሃብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።
____________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide