ነሃሴ ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጽያ ሃይማኖቶች ተቋማት ጉባዔ ዛሬ ከቀትር በሁዋላ በአ/አ አምባሳደር ቲያትር አካባቢ በሚገኘው ጽ/ቤቱ
ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አክራሪነትን ለመቃወም የፊታችን እሁድ ነሃሴ 26 ቀን በመስቀል አደባባይ ሰልፍ
መጥራቱን አስታወቀ፡፡
በዕለቱ ሰማያዊ ፓርቲ ሁለተኛ ሰልፉን በመስቀል አደባባይ ለማድረግ በይፋ ለአስተዳደሩ አሳውቆ ምላሽ እየተጠባበቀ የሚገኝ ሲሆን ምናልባት የሃይማኖት ተቋማቱ ሰልፍ ለማካሄድ መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ የሰማያዊ ሰልፍ በዕለቱ ላይፈቀድ ይችላል የሚል ግምት አሳድሮአል፡፡
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኃይማኖቶች ተቋማት ጉባዔ ጋር በመተባበር “ኃይማኖቶች አብሮ የመኖር እሴት በማጎልበትና ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር የሀገራችንን ሕዳሴ ጉዞ ለማሳካት እንረባረባለን” በሚል መሪ
ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከነገ ነሐሴ 21–23/2005 ዓ/ም የሚቆይ ጉባዔ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ያካሂዳል፡፡ ይህ ጉባዔ ከተዘጋ በኃላ በተለይ የሕዝበ ሙስሊሙን የመብት ጥያቄ ከአክራሪነት ጋር አስተሳስሮ የሚያወግዝ ሰልፍ ነሐሴ 26 ይካሄዳል፡፡
በሰልፉ በርካታ ሰው እንዲገኝ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ለመንግስት ሰራተኞች፣ ለፓርቲ አባላት፣ ለሴቶች ሊግ፣ ለወጣቶች ሊግ እንዲሁም በጥቃቅን እና አነስተኛ ለተደራጁ ማህበራት አባሎችና በኮብል ስቶን የሰለጠኑ ወጣቶች የግዳጅ መመሪያ ተላልፏል፡፡
ጥሪ የደረሰቸው ሁሉ በሰልፉ ላይ ለመገኘት ቀደም ብለው በፊርማቸው ያረጋግጣሉ።
ከዚህም በለይ በሰልፉ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትም እንዲሳተፉ መንግስት ጫና በማድረግ ላይ እንደሆነ በቤተ ከህነትና ባኢስልምና ገዸዮች ያሉ ምንጮች ጠቁመዋል።
ከሃይማኖት ተቋማት በተጨማሪ የተለያዩ የግል ድርጅቶች በተለይም የጅምናስቲክ፣ የማርሻል አርትና የቴኳንዶ ስልጠና የሚሰጡ ድርጅቶች ሰልጣኞች ተማሪዎቻቸውን በሰልፉ ይዘው እንዲገኙ በየወረዳው አስተዳዳሪዎች ትእዛዝ ተላልፎላቸዋል፡፡
ከየክፍለ ከተማው አስከ አስር ሺ ሰው እንዲሳተፍበት በተላለፈው መመሪያ መሰረት የወረዳ ቢሮዎች ኮታውን ለመሙላት ይሄን ሳምንት ሙሉ ጊዜያቸውን ለዚሁ ስራ በመስጠት ከፍተኛ የቅስቀሳ እና የግደጅ ስራ ለመስራት ተዘጋጅተዋል፡፡
መንግስት በክልል ከተሞች ሲያካሄደው እንደነበረው ሁሉ ለዚህ ሰልፍም ከፍተኛ ባጀት መመደቡ ታውቋል።