ኢህአግ በሁመራ አካባቢ ጥቃት መፈጸሙን ገለጸ

ግንቦት ፳፯ (ሀያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት በሉግዲና በበረከት ተከታታይ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

በግንቦት 25-2005 ዓ.ም በሁመራ ልዩ ስሙ በረከት በተሰኘ ስፍራ ከመከላከያ ሰራዊት  35ኛ ክፍለጦር እና ከሚሊሻ ሰራዊት ጋር በተከታታይ በስምንት/8/ ዙር ፋታ የለሽና እልህ አስጨራሽ ውጊያ 148 ሙት፣ 374 ቁስለኛ፣ 31 ክላሽንኮፍ ጠመንጃ፣  47 የእጅ ቦንብ ፣2 ስናይፐር፣ 3 መትረየስና የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን መማረኩን አስታውቋል።

በግንቦት 24 እና  25-2005 ዓ.ም በተካሄደው ውጊያ ደግሞ በድምሩ 192 ሙት፣  440 ቁስለኛ ቁጥራቸው የበዛ ተተኳሽ መሳሪያዎችን ከነትጥቃቸው መማረክ መቻሉን ገልጿል። ኢሳት የመንግስትን አስተያየት ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም።