ግንቦት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ገዢው ፓርቲ የግንቦት20 በአልን ምክንያት በማድረግ ባወጣው መግለጫ ተቃዋሚዎች እያሳደሩ ያለውን ተጽእኖ በዝርዝር አቅርቧል።
ኢህአዴግ በመግለጫው ” አገሪቱ የተያያዘችው ፈጣን ልማትና የዳበረ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ያስደነገጣቸው የጥፋት ሀይሎች ከውጭ ሆነው ለኢትዮጵያ ድጋፍ አታድርጉ፣ ብድር አትፍቀዱ ከማለት ጀምሮ ከሻዕብያ መንግስት ስልጠናና ምክር በመውሰድ በሽብር ስራ ላይ መሰማራታቸውን፣ በአገር ውስጥ ደግሞ የሀይማኖት፣ የኑሮ ውድነቱንና ሌሎች አጀንዳዎችን በማራገብ ላይ ይገኛሉ” ብሎአል።
ኢህአዴግ የእነዚህን አፍራሽ ሀይሎች ተልእኮ በቸልታ እንደማይመለከት ፣ ህዝቡም የጥፋት ሀይሎችን በጽናት ለመታገል ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርቧል።
ከኢህአዴግ ምክር ቤት የተሰጠው መግለጫ ሀገሪቱ በፈጣን የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ብትገኝም ድህነትና ኋላቀርነት፣የኑሮ ውድነት፣በህብረተሰቡ ውስጥ የሚታየው በአቋራጭ የመክበር አስተሳሰብና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሥርዓቱን የሚፈታተኑ ችግሮች መሆናቸውን አብራርቷል።
እነዚህ ችግሮች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተደደርን በማስፈን እንደሚፈቱ ኢህአዴግ ፅኑ አቋም እንዳለው ያብራራው መግለጫው አጣዳፊ የሆኑ የህዝቡን የኑሮ ውድነት ችግሮች ለመፍታት መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብና የሥራ ዕድሎችን በስፋት በመፍጠር የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ለማሳደግ ኢህአዴግ ትኩረት ሰጥቶ በመረባረብ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ኢህአዴግ በአንድ በኩል ተቃዋሚዎች ህዝብን በሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየቀሰቀሱብኝ ነው በማለት ቢናገርም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ድህነትና ሁዋላ ቀርነት፣ የኑሮ ውድነትና በህብረተሰቡ ውስጥ የሚታየው በአቋራጭ የመበልጸግ እና የመልካም አስተዳዳር ችግሮች ስርአቱን የሚፈታተኑ ችግሮች ሆነዋል ይላል።
ኢህአዴግ የመልካም አስተዳዳር እጦት፣ የኑሮ ውድነትና ስርአጥነት የመሳሰሉት ችግሮች የስርአቱ ፈተና ሆነዋል በማለት ለማመን ከተገደደ፣ በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች እነዚህን ችግሮች ያራግባሉ በማለት ክስ ማሰማቱ እርስ በርስ የሚቃረን ነው ሲል ዘጋቢያችን ገልጧል። እነዚህ ችግሮች ባይኖሩና ተቃዋሚዎች ፈጥረው ቢያወሯቸው የኢህአዴግ ወቀሳ ትክክል ይሆን ነበር የሚለው ዘጋቢያችን፣ አሁን ግን ኢህአዴግ ችግሮች በስፋት መኖራቸውን ካመነ በሁዋላ ተቃዋሚዎች እነዚህን ችግሮች እያራገቡ ነው በማለት ክስ መሰንዘሩ ኢህአዴግ የገባበትን አጣብቂኝ ያሳያል ብሎአል።
በሌላ ዜና ደግሞ አቶ መለስ የግንቦት20ን በአል በማስመልከት ምንም ቃል ሳይተነፍሱ ያሳለፉበት አመት ቢኖር የዘንድሮው ነው። አቶ መለስ እስካሁን በቴሌቪዥን ወይም በራዲዮ ወይም በጋዜጦች ቀርበው ዘወትር ያደርጉ እንደነበረው ቃለምልልስ አልሰጡም። አቶ መለስ ያለፈውን ሳምንት ያሳለፉት በ21 አመት የስልጣን ዘመናቸው አጋጥሞአቸው የማያውቅ ተቃውሞ አስተናግደው ነው። በጋዜጠኛ አበበ ገላው እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከደረሰባቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ያገገሙ የማይመስሉት አቶ መለስ፣ ወደ ስልጣን ኮርቻ ያመጣቸውን ግንቦት20ን ሳይዘክሩ መቅረታቸው መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide