ኢህአዴግ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አለመሳካቱን አመነ

ኀዳር (አምስት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-ዘንድሮ የሚጠናቀቀው የኢህአዴግ የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን የተለጠጠ ዕቅድ በግብርና ዘርፍ መዳከም ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱን ኢህአዴግ ለመጀመሪያ ጊዜ  በይፋ አመነ፡፡

ኢህአዴግ «አዲስ ራዕይ» በተሰኘው በርዕዮተ ዓለም ልሳኑ የመስከረም- ጥቅምት 2007 ዓ.ም ዕትም ላይ የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአራት ዓመታት አፈጻጸም አስመልክቶ ባሰፈረው ሐተታ እንደጠቆመው ለጥጦ የያዘውን ዕቅድ ማሳካት እንዳልቻለ በማስቀመጥ አባላትና ደጋፊዎቹን አጽናንቷል፡፡

ግንባሩ ባለፉት አራት ዓመታት በግብርና ፣በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት ዘርፎች አመርቂ ውጤት መገኘቱን በደፈናው ካስቀመጠ በሃላ ግንባሩ የተለጠጡ ዕቅዶችን አንግቦ የተነሳና ለማሳካትም ወቅቱ የፈቀደውን ያህል የተንቀሳቀሰ
ቢሆንም ከሞላ ጎደል መሠረታዊውን የዕድገት ምጣኔ እንጂ በተለጠጠ አኳሃን የነደፈውን ግብ ማሳካት ሳይችል መቅረቱን አምኗል፡፡ «በራሳችን ተነሳሽነት ለጥጠን ያስቀመጥነው ግብ ላይ ባለመድረሳችን ዛሬም የምንቆጭና ለነገ በእልህና በላቀ ወኔ መነሳሳት እንዳለብን የምንገነዘብ ቢሆንም በአራቱ ዓመታት በርብርብ የተመዘገበው ውጤት የሚያኮራ ነው» ሲል ይጠቅሳል፡፡

ያለፉት አራት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ በአማካይ 7 ነጥብ 15 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት እንዳስመዘገበ የሚጠቅሰው አዲስራዕይ ይህ የዕድገት ምጣኔ በማንኛውም መልኩ ካስቀመጥነው የ14 ነጥብ 9 በመቶ የተለጠጠ ዕድገት ምጣኔ ብቻ ሳይሆን ከመሰረታዊው የ11 በመቶ የእድገት ምጣኔም ትርጉም ባለው ደረጃ ዝቅ ያለ ነው ሲል በይፋ ያምናል፡፡

የግብርና ዘርፉ ከሰባት እስከ ስምንት በመቶ ሲያድግ ኢኮኖሚው ወደ 10 በመቶ ማደጉን፣ የግብርናው ዕድገት ወደ 9 በመቶ ከፍ ሲል ደግሞ ኢኮኖሚው 11 ነጥብ 4 በመቶ ማደጉን  አስታውሶ የግብርና ዘርፉ ባቀድነው መሠረት ከ11 አስከ 15 በመቶ ማደግ ቢችል ኖሮ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ወደተለጠጠው ግብ በተጠጋ ነበር በማለት ያስቀምጣል፡፡የግብርና ዕድገቱ አጠቃላዩን የዕድገት ምጣኔ ዝቅ ወይንም ከፍ የማድረግ ውጤት ያለው መሆኑ እንደተጠበቀ የሚዋዥቅ ዕድገት የነበረ መሆኑ አጠቃላዩን አገራዊ ፈጣን ዕድገት መጠነኛ መዋዥቅ ያስከተለ ነበር ብሎአል፡፡ በአራቱ ዓመታት የግብርና ልማት ዕድገት የተመዘገበው ውጤት በተከታታይ ፈጣን አይደለም ያለው የአዲስራዕይ ዝቅተኛ ዕድገት የተመዘገበበትን 2004 ዓ.ም በአብነት በመውሰድ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ  ፍጥነታችን ወደታች የወረደ ነበር ሲል ድክመቱን አስቀምጦአል፡፡

መጽሔቱ አያይዞም «በዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አራት ዓመታት ባለሁለት አሀዝ አማካይ ዕድገት ብናረጋግጥም የተለጠጠውን ግብ ያላሳካንበት ሆነ  እድገታችን ወደ 8 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ ያለበትና የመዋዥቅ ገጽታ የተላበሰበት ውጤት የሚያመለክተው የፖለቲካ ጥራታችን በተገቢው ደረጃ ያልተጠበቀባቸው ሒደቶች ውስጥ ማለፋችን ነው ካለ በሁዋላ የልማት ሥራችን በከፍተኛ ፍጥነት የማደግ ውጤት እንዲያስከትል በተሟላ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ጠንክረን በላቀ ዲሲፒሊን መንቀሳቀስ ሲገባን በነዚህ መሠረታዊ አቅሞቻችን ላይ መላላት ተፈጥሮ ነበር» በማለት የኢህአዴግን ውስጣዊ ችግር አመልክቷል፡፡

የአምስት አመቱ እቅድ በታቀደበት ወቅት የተለያዩ ምሁራንና በውይይቱ ተሳተፉ የተባሉ ሰዎች እቅዱ ተለጥጧል በሚል መተቸታቸውን  በወቅቱ በስልጣን ላይ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ተናግረዋል

ትችቱን አለመቀበላቸውን የገለጹት አቶ መለስ ከተቻለ 15 በመቶ ካልተቻለም 11 በመቶ እድገት ካገኘን ትልቅ ስኬት ነው በማለት የህዝቡንና የምሁራኑን አስተያየት ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

ብቸኛው የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ እቅዱ በቂ ዝግጅት ያልተደረገበትና ለፖለቲካ ድጋፍ ማስገኛ ተብሎ በስሜት የተዘጋጀ መሆኑን በጽኑ በመተቸት እቅዱ ባይሳካ ጠ/ሚኒስትሩ በሌሎች አገሮች እንደሚታየው ስልጣን ይለቁ ይሆን ሲሉ ጠይቀዋቸዋል

አቶ መለስ 11 በመቶ እድገት ቀርቶ 7 በመቶ እድገት ማግኘት ትልቅ ነገር በመሆኑ፣ ኢህአዴግ ስልጣን እንደማይለቅ ምላሽ መስጠታቸው ይታወቃል።

ለአቶ መለስ ድጋፋቸውን የገለጹት ሌላው የፓርላማ አባል ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ እቅዱ መሳካትና አለመሳካቱን የዛሬ አምስት አመት እንገናኝና እንየው ሲሉ አቶ ግርማ ሰይፉን ተችተዋል

የተለያዩ ምሁራን ኢትዮጵያ ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም እቅዱን ለመተግበር በቂ የሆነ ገንዘብ ላታገኝ ትችል ይሆናል በማለት ስጋታቸውን በወቅቱ ቢገልጹም አቶ መለስ ስጋቱን አጣጥለውታል

አቶ ሃይለማርያም የአምስት አመቱ የልማት ግብ በአብዛኛው ተሳክቷል በማለት በቅርቡ ለፓርላማው ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።