ኢሳት ዜና፡- ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመልከተው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመድረክ አባላት ላይ የሚያደርገውን ማሳደድ አጠናክሮ ቀጥሎበታል።
የአረና ትግራይ አባል የሖነው አማረ ተወልደ በሁመራ አካባቢ የድርጅቱን ወረቀት ሲበትን ተገኝቷል በሚል ሰበብ ለበርካታ ቀናት በቁጥጥር ስር ከዋለ በሁዋላ በመጨረሻም ንብረቱንና እቃዎቹን ተቀምቶ በሳምንቱ መጨረሳ ተለቋል።
በተመሳሳይ ዜናም የዚሁ የአረና ትግራይ አባል የሆኑት አቶ አያሌው በዬነ በሽሬ ከተማ የፓርቲውን ወረቀት ሲበትኑ ተገኝተዋል በሚል ሰበብ በቁጥጥር ስር ውለዋል። መምህር ጎይቶም ጸጋየ የተባሉት ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ናቸው ተብለው ከስራቸው እንዲባረሩ ተደርገዋል።
ለኢሳት የደረሰው ዜና አክሎ እንደሚያመለክተው አቶ መለስ ዜናዊ የመድረክ በርካታ አመራሮች የአሸባሪ ድርጅት አባላት ናቸው የሚል ክስ በፓርላማ ፊት መናገራቸውን ተከትሎ፣ ካድሬዎቻቸው በመድረክ አባላት ላይ የሚያደርሱትን ወከባ አጠናክረው ቀጥለዋል።
አቶ አያል ጌታነህ የተባሉ በምስራቅ ጎጃም የሚኖሩ የአንድነት ፓርቲ አባልም እንዲሁ ከማንኛውም ማህበራዊ ግንኙነት ለአንድ አመት ታግደው እንዲቆ ዩ የወረዳው ፍርድ ቤት ወስኖባቸዋል።
በተመሳሳይም በዚሁ ዞን ውስጥ የሚኖሩት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዘመድያ አገዘ የተባሉት የፓርቲው አባሎች ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ የደረሱበት አልታወቀም።
አቶ ሻምበል የሽዋስ ይሁን የተባሉ የምእራብ ጎጃም ነዋሪም ካለፉት ሶስት ሳምንታት ጀመሮ የደረሱበት አለመታወቁን የደረሰን መረጃ አመልክቶ፣ መምህር ሙሳ ኢብራሂም የተባሉ የዚሁ ፓርቲ አባልም በድብደባ ህይወታቸው አልፎአል።
መድረክ ከቅርብ ጊዜ ወዲሂ ስልጣንን ያለተቀናቃኝ የሙጥኝ ላለው የመለስ መንግስት ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መምጣቱ ይነገርለታል። አንዱአለም አራጌ፣ ኦልባና ሌሊሳና በቀለ ነገአን የመሳሰሉት የመድረክ አመራሮች በአሸባሪነት ስም ለእስር ተዳርገዋል።
መድረክ በቅርቡ ከቅንጅት ወደ ግንባር መሸጋገሩ የገዢውን ፓርቲ የስጋት መጠን ከፍ በማድረግ ተጨማሪ ወከባ እንዲፈጠር ሳያደርገው እንዳልቀረ ዘጋቢያችን ጠቁሟል።