ኢህአዴግ  ለምርጫው ዝግጅት እንዲሆን በማለት በብሄር ለተደራጁ ፓርቲዎች 200 ሚሊዩን 349 ሺ 231 ብር  ፈሰስ አደረገ፡፡

ጥር ፲፬(አስራ አራት ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የድርጅቱ ምንጮች ለኢሳት እንደጠቆሙት፤ በመጀመሪያው ዙር ፈሰስ የተደረገው ይህ ገንዘብ ለቲሸርት ፤ ለኮፍያ ፤ እና ለበራሪ ወረቀቶች ህትመት  የሚውል ነው ተብሏል፡፡

ለፕሮሞሺን ስራ አገልግሎት የሚውል ተብሎ በብሄር ለተደራጁ ድርጅቶች ፈሰስ  ከተደረገው ከዚህ ገንዘብ ባሻገር ለአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ማለትም ለህወሀት፣ ለብአዴን፣ለኦህዴድ እና ለደኢህዴግ  5 ሚሊዮን  87 ሺህ 307 ብር ከ75 ሳንቲም  በየአካውንታቸው ገቢ መደረጉን ምንጮቹ አመልክተዋል።

ኢህአዴግ ላባል ድርጅቶቹ ያከፋፈለውን ይህን ገንዘብ <<ከአባላት ክፍያ ያሰባሰብኩት ነው>> ማለቱም ተሰምቷል። ኢህአዴግ ከዚህም በላይ ከግንቦቱ ምርጫ ጋር በተያያዘ  ከበለሃብቱ  ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ እቅድ ማውጣቱና ይህንንም እቅዱን  በዚሁ በጥር ወር አጋማሺ ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ታውቋል።

የሚሰበሰበው ገንዘብ በኢህአዴግ  ግምገማ<< የምርጫው የስጋት ቀጠናዎች >> ተብለው  በተለዩት በአማራ ፤ ኦሮምያ፤ ትግራይ እና ደቡብ ክልሎች   ድጋፍን ለማጠናከር ይውላል መባሉንም የምንጮቻችን መረጃ ያመለክታል።