ዶናልድ ፔይን በጠና ታመዋል

የካቲት 26 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ እውነተኛ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባ ዘንድ ያለማሳለስ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩት አፍሪካዊ አሜሪካዊው ኮንግረስ ማን ዶናልድ ፔይን፤ በጠና መታመማቸው ተዘገበ።

በብዙሀን ኢትዮጵያውያን ዘንድታላቅ ስፍራ ያላቸው የኒው ጀርሲው ተወካይና የዲሞክራቲክ ፓርቲው  አባል ዶናልድ ፔይን የታመሙት በአንጀት ካንሰር  ነው።

እንደ “ፖሊቲኮ” ብሎግ ዘገባ፤ የአንጀት ካንሰሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ህመሙ በዶናልድ ፔይን ላይ ያየለባቸው ሲሆን፤ ህይወታቸው እጅግ አሣሳቢ የሆነ ደረጃ ላይ ደርሷል።

የሥራ ባልደረቦቻቸውና የፓርቲያቸው አባላት በቅርቡ ኮንግረስ ማን ፔይን ህክምና በሚከታተሉበት በጆርጅ ታውን ሆስፒታል ተገኝተው ጎብኝተዋቸዋል።

አንድ ስማቸውን ያልገለጹና ለኒው ጀርሲ ተወካዮች ልዑካን ቅርበት ያላቸው ምንጭ፦“ዶናልድ ፔይን ወደ ህይወታቸው ፍፃሜ በመቃረባቸው የኒው ጀርሲ ተወካይ ልኡኮች አዝነዋል” በማለት ለካፒቶል ነግረውታል።

የፔይን ልጅ  በሰጠው አስተያዬት፦” እኛ ተስፈኞች ነን ። ነገር ግን  ህመሙ  ካንሰር ነው “ ብሏል።

የ 77 ዓመቱ ዶናልድ ፔይን የጋርደን ስቴት የመጀመሪያው አፍሪካዊ አሜሪካዊ ኮንግረስ ማን መሆናቸውን ፖሊቲኮ አስታውሷል።

ባለፈው ወር የሥራ ፈቃድ የወሰዱት ዶናልድ ፔይን ለመጪው ምርጫ ለመወዳደር እቅድ እንደነበራቸውም ተጠቁሟል።

እስካሁን  የዶናልድ ፔይን ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት መግለጫም ሆነ አስተያዬት አልሰጠም።

የዶናልድ ፔይን በጠና መታመም መሰማቱ  ከ አሜሪካውያን አልፎ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ጭምር ያሳዘነ ሆኗል።

ይህ ለኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ  ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን ሆኖ ማየት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አስደንጋጭና አሳዛኝ ዜና ነው ያሉት የሆላንዱ ነዋሪ አቶ አሰግድ ያሬድ፤ ለኛ ፔይንን ማጣት ብዙ ነገር እንደማጣት በመሆኑ ፈውስ ይመጣላቸው  ዘንድ ልንፀልይላቸው ይገባል ብለዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide