“አገሪቷ በማን እየተመራች እንደሆነ አለመታወቁ አሣስቦኛል” ሲል መኢአድ ስጋቱን ገለጸ

ሐምሌ ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአሁኑ ጊዜ አገሪቷን እየመሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ናቸው መባሉ እንዳልተዋጠለት እና በትክክል ይች አገር በማን እየተመራች እንደሆነ አለመታወቁ እንዳሣሰበው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ገለጸ።

ይህ የመኢአድ  ስጋት የተገለጸው፤ ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህይወት እንደሌሉ የሚያመላክቱ ዘገባዎች እየወጡ ባሉበት ባሁኑ ጊዜ የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምዖን ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና አሁንም የአገሪቱ መሪ እርሳቸው እንደሆኑ በተደጋጋሚ መግለፃቸው ይታወሳል።

መኢአድ እንዳለው፦ አገሪቱን እየመሩ ያሉት አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው ተብሎ መገለፁ፤ የህገመንግስቱን የህግ ክፍተት የሚያሳይ ነው።

“የኢትዮጵያ ህዝብ መሪው ሲታመምና ሳይኖር በማን እንደሚመራ የማወቅ መብት አጥቷል” ያሉት የፓርቲው አመራሮች፤ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱን ማን እንደሚመራትም አናውቅም፡፡”ብለዋል።

የመ ኢአድ አመራሮች አክለውም፦” የጠ/ሚኒስትሩ ሥራ ደቂቃ በደቂቃ ውሳኔ የሚጠይቁና ፊርማ የሚያስፈልጓቸው ጉዳዮች አሉበት፡፡ አቶ በረከት ማነው የሚመራን ተብለው ሲጠየቁ ፤<ሆስፒታል የተኙት አቶ መለስ ናቸው> ማለታቸው ፤ የህገመንግስቱን የህግ ክፍተት የሚያሳይ ነው፡፡ ክፍተቱ፤ምክትል ጠሚኒስትሩ ተክተው የመሥራት ሥልጣን እንደሌላቸው ያሳየ ነው። ስለሆነም  በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ የሚመራውን አያውቅም” ብለዋል።

በሌላ በኩል መንግስት እጁን ከሃይማኖት ላይ እንዲሰበስብ ጥሪውን መኢአድ ጥሪ ማቅረቡን የፍኖተ-ነጻነት ዘገባ ያመለክታል።

የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ወንድምአገኝ ደነቀው፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ወይዘሪት መሶበ ወርቅ ቅጣው እና  የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው አቶ አበባው መሐሪ በጋራ በመሆን በሰጡት በዚሁ  መግለጫ፤-“ የኢህአዴግ መንግስት የሃይማኖት ተቋማትን በካድሬዎች ለመምራት ካለው  አቋም በመነሳት እጁን በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ አስገብቶ ሃይማኖቶችን እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚያከናውነውን ተግባር ማቆም አለበት” ብሎአል፡፡

 

“በአገሪቱ ውስጥ አሸባሪነት ስለመኖሩ ማረጋገጫ የለም” ያሉት የመኢአድ አመራሮች፤ “የሙስሊሙን ህብረተሰብ ለመከፋፈል መንግስት እያከናወነ ያለውን ድርጅታዊ ሥራ ማቆም አለበት” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የመኢአድ አመራሮች አያይዘውም፦ “ኢህአዴግ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ ሙስሊሙን ህብረተሰብ ላነሳው ጥያቄ ፦” መሪዎቻችሁን በቀበሌ ምረጡ” የሚል መልስ መሰጠቱ፤በግልጽ መንግስት በሙስሊም ሃይማኖት ውስጥ ለመዘርጋት የፈለገውን እጅ የሚያሳይ ነው” ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በዋልድባ ገዳም ሦስት ቤተክርስቲያኖችን ለማፍረስ መወሰኑ እና  ምዕመናን በሃይማኖቱ ሥርዓት መሠረት ዓመታዊ ክብረበዓል እንዳያከብሩ መከልከሉ ፤ ኢህአዴግ በሃይማኖት ዙሪያ እየተከተለ ያለውን ጣልቃ ገብነት የሚያሳይ ነው፡፡” ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል-የመኢአድ አመራሮች።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide