አዴፓ በስግብግብነት የታሪክ እና የስልጣን ሽሚያ ውስጥ እንደማይገባ ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 16/2011)የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ በስግብግብነት የታሪክ እና የስልጣን ቦታ ሽሚያ ውስጥ አይገባም ሲሉ የፓርቲው የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ገለጹ

አዴፓ በፓርቲው የሁለት ቀናት የማዕከላዊ ኮሚቴ  ስብሰባ የውይይት ጭብጦችና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ዶክተር አምባቸው መኮንንን የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሲመርጥ ዘጠኝ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚዎችንም ለይቷል።

የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ በባህርዳር ከተማ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ምክትል ሊቀ መንበሩን እና አዳዲስ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚዎችን መርጧል። ማዕከላዊ ኮሚቴው ዶክተር አምባቸው መኮንንን የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሲመርጥ ዘጠኝ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚዎችንም ለይቷል። በዚሁም መሰረት ቀደም ሲል ከነበሩት ዘጠኝ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባላት ሁለቱን በማንሳት አቶ ላቀ አያሌውንና አቶ ዮሀንስ ቧያለውን ተክቷል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሜቴ በክልሉ ያለውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ለሁለት ቀናት ገምግሟል።

ለውጡን ለማስቀጠል የሚረዱ ተግባራት ጥሩ ቢሆኑም በሂደቱ ግጭቶች እና የሰላም ውስንነቶች መፈጠራቸውንና አመራሩን የማጠናከር ሥራ መሠራቱንም የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ገልጸዋል። አዴፓ በለውጡ መንገድ የተስተዋሉ ቀውሶች ምጣኔ ሀብቱ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን ፓርቲው መገምገሙንም ነው የተናገሩት።  የተጀመረው ለውጥ ፍጥነቱን እንዲቀጥል በማድረግ ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ቀናት በባሕር ዳር እና ደሴ የታዩ ችግሮች ከኅብረተሰቡ የሰላም ፍላጎትና የንቃት ደረጃ የማይመጥኑ ደካማ ድርጊቶች እንደነበሩ ነው የተናገሩት፡፡

አቶ ዮሐንስ በአዴፓ እና ኦዴፓም ሆነ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታፍኖ የነበረ በመሆኑ የልዩነት ሐሳብ ቅራኔ ይመስላል፤ ግን ጤናማ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በእኛ እና ኦዴፓ መካከል ልዩነት የተፈጠረ መስሏቸው የሚቦርቁም አሉ፤ ለእነዚህ መርዷቸውን ንገሯቸው፡፡ እኛ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕድል ብሩህ ለማድረግ እየሠራን ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹ከትግራይ መንግሥት ጋርም ዘራፊዎችን አሳልፎ አለመስጠቱ እንጂ ሌላ ቅሬታ የለንም›› ብለዋል።፡

‹‹አዴፓ በስግብግብነት የታሪክ እና የቦታ ሽሚያ ውስጥ አይገባም፡፡ ከሌሎች ሕዝቦች የተለዬ ጥቅም ለአማራ በማምጣት ለሌሎች ስጋት እንዲታይም አይሰራም›› ነው ያሉት፡፡

አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ከተማ እንደሆነች የኢህአዴግ እህት ፓርቲዎች እንደሚያምኑ በመግለጽ ይህን ባለማመን የኃይል እርምጃን የሚያስተናግድ የፖለቲካ ርዕዮት አንደማይኖርም የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ገልጸዋል።