ታህሳስ 20 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ትናንት በኦሮሞና በትግራይ ተማሪዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የፌደራል ፖሊሲ በስፍራው በመገኘት ግጭቱን አስቁሟል።
ይህንን ተከትሎም በርካታ ተማሪዎች በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ወደ እስር ቤት የተወሰዱ ሲሆን የኦሮሞ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ሲጮሁ፣ የመብት ጥያቄዎችን በማንሳት ሲጠይቁ እንደነበር የአይን እማኞች ተናግረዋል።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ መምህር ግጭቱ የብሄር ግጭት መሆኑን ለኢሳት ተናግረዋል።
ዛሬ በግቢው ውስጥ የተለያዩ ማስጠንቀቂያ አዘል ማስታወቂያዎች መለጠፋቸውንም ለማወቅ ተችሎአል። በተጨማሪም መምህራን ወደ ክፍል በማይገቡ ተማሪዎች ላይ ቁጥጥር እንዲያደርጉ እና ሪፖርታቸውንም ለዩኒቨርስቲው ባለስልጣናት እንዲያስተላልፉ ታዘዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከዘር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ግጭቶች እየጨመሩ መምጣታቸው ኢትዮጵያ በአስፈሪ የታሪክ አጋጣሚ ውስጥ እንደምትገኝ ያመለክታል የሚሉ አስተያየቶች በተደጋጋሚ ይቀርባሉ።
ገዢው ፓርቲ በቅርቡ የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ማክበሩ ይታወቃል።