አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢትዮጵያውያን በሚሰጠው የቪዛ ቁጥር ላይ የተጣለ ገደብ አለኖሩን አስታወቀ

ኢሳት (መጋቢት 21 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢትዮጵያውያን በሚሰጠው የቪዛ ቁጥር ላይ የተጣለ ገደብ አለኖሩን አስታወቀ።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ማሻሻያ አድርገው ያቀረቡትንና በፍርድ ቤት ዳግም ውድቅ የተደረገባቸውን የኢሚግሬሽን መመሪያ ተከትሎ በተለያዩ መንገዶች ለኢትዮጵያ በሚሰጥ የቪዛ ኮታ ላይ ቅነሳ እንደተደረገ ተደርጎ መረጃ በመሰራጨት ላይ መሆኑን ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ይኸው ኢትዮጵያን በተመለከተ እየተነገረ ያለውና በመሰራጨት ላይ የሚገኘው መረጃ “የውሸት ነው” ሲል የአሜሪካ ኤምባሲ ገልጿል።

ለቪዛ ጠያቂዎች እየተደረገ ያለው መስተንግዶም በተለመደው ሁኔታ ቀጥሎ እንደሚገኝ ያመለከተው ኤምባሲው፣ በቪዛ ቁጥር ላይ የተደረገ ማሻሻያ አለመኖሩን ልናረጋግጥ እንወዳለን ሲል ለህዝብ ባሰራጨው መልዕክቱ አስፍሯል።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ የመግቢያ ቪዛ ኖሯቸው ማደስ የሚፈልጉ ግለሰቦች እንደከዚህ በፊት የቪዛ የማደስ ጥያቄያቸው ቪዛቸው ከአንድ አመት በፊት ከመጠናቀቁ በተለመደው መልኩ ማደስ እንደሚችሉ አስታቋል።

ይሁንና የአሜሪካ የቪዛ መስጫ ክፍል ቪዛ ማደስ የሚፈልጉ ሰዎችን በድጋሚ ቃለመጠይቅ እንዲያደርጉ ሊጠይቅ እንደሚችል አክሎ ገልጿል።

ዕድሚያቸው ከ14 እስከ 79 የሆናቸው የቪዛ አመልካቾችም ከተወሰኑ የቪዛ አይነቶች ውጭ ጥያቄያቸውን በአካል በመገናኘት ማቅረብ እንደሚኖርባቸው ኤምባሲው አስረድቷል።

የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሃገሪቱን የጸጥታ ሁኔታ ለማጠናከር እንዲሁም የሽብር ጥቃትን ለመከላከል ይረዳል በማለት አዲስ የኢሚግሬሽን ደንብን ተግባራዊ ለማድረግ ቢሞክሩም ሃሳቡ ለሁለተኛ ጊዜ በፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።

ፕሬዚደንት ትራምፕ በበኩላቸው ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ በማቅረብ ውሳኔው እንዲቀለበስ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ይሁንና የይግባኝ ጥያቄው መቼ እንደሚቀርብ የተገለጸ ነገር የሌለ ሲሆን፣ በርካታ የአሜሪካ የህግ አካላት የፕሬዚደንቱ መመሪያ የሃገሪቱን ህግን የሚጻረር ነው በማለት ተቃውሞን አሰምተዋል።

ኢራን፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ሶሪያና የመን በሁለተኛው ዙር በአዲሱ ዕገዳ ተካተው የነበሩ ሲሆን፣ ኢራቅ ከእገዳው እንድትወጣ ተደርጓል።

የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ተሻሽሎ የቀረበው መመሪያ ከመጀመሪያው የተለየ እንደሆነ ቢገልጽም የህግ አካላት ማሻሻያው አሁንም ቢሆንም አሳማኝ አይደለም ሲሉ ውድቅ እንዲሆን ወስነዋል።

ፕሬዚደንቱ በተመሳሳይ መልኩ በጤና ኢንሹራንስ ላይ ያቀረቡት ሃሳብ በበርካታ የሃገሪቱ የምክር ቤት አባላት ዘንድ ድጋፍ በማጣቱ የቀድሞ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ተግባራዊ ያደረጉት እና ኦባማ ኬር በመባል የሚታወቀው ኢንሹራንስ ቀጣይ እንዲሆን ተደርጓል።