በሳውዲ በህገወጥ የሚኖሩ ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በ90 ቀናት ከአገር እንዲወጡ ተጠየቁ

ኢሳት (መጋቢት 21 ፥ 2009)

የሳውዲ አረቢያ መንግስት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ከሶስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቀጣዮቹ 90 ቀናቶች ውስጥ ከሃገሪቱ እንዲወጡ አሳሰበ።

ይኸው የ90 ቀን ገደብ ረቡዕ የተጀመረው ሲሆን፣ ዕርምጃው በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት እንደሆነ ተመልክቷል።

መንግስት በበኩሉ የሳውዲ አረቢያ ውሳኔ የሚመለከታቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ገልጾ፣ ኢትዮጵያውያኑ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከሃገሪቱ እንዲወጡ ጠይቋል።

የሳውዲ አረቢያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የሃገር ውስጥ ጉዳዩ ሚኒስትር ሞሃመድ ቢን ናኢ’ፍ በተቀመጠው የ90 ቀን የጊዜ ገደብ ከሳውዲ አረቢያ በፈቃደኝነት የሚወጡ ሰዎች ምንም አይነት ቅጣት ተግባራዊ እንደማይደረግባቸው መግለጻቸውን ሳውዲ ጋዜት ዘግቧል።

ወደ ሃገሪቱ ለሃይማኖታዊ ስነስርዓት፣ ጉብኝትና በተለያዩ ምክንያቶች ገብተው የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በስራ ላይ የሚገኙና ፈቃዳቸው ያለቀባቸው ሰዎች በጊዜ ገደቡ በፈቃደኝነት መውጣት እንዳለባቸው ሚኒስትሩ አስታውቋል።

ከአራት አመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚሁ ዘመቻ ከሶስት ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች መመሪያው እንደሚመለከታቸው ታውቋል።

ሳውዲ አረቢያ ለመጀመሪያ ዙር ያስተላለፈችው ተመሳሳይ ውሳኔ ተከትሎ ከ100ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን በግፍ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ የሚታወስ ነው።

ከረቡዕ ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው በዚሁ የጊዜ ገደብ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ቤት እንዲመለሱ ይጠበቃል።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው ሃገሪቱ ከ90 ቀናት በኋላ ልትወስድ የምትችለውን በሃይል የማስወጣት ዕርምጃ ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ሳውዲ አረቢያ በመጀመሪያ ዙር በወሰደችው በሃይል የማስወጣት ድርጊት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች መሞታቸውንና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው ይታወሳል።

የ90 ቀን የጊዜ ገደቡ መጠናቀቅ ተከትሎ የሳውዲ አረቢያ መንግስት የጸጥታ ሃይልን በማቋቋም መመሪያው የሚመለከታቸው ግለሰቦች ላይ ዕርምጃን እንደሚወስድ የሳውዲ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

መቀመጫቸውን በሳውዲ አረቢያ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት ኢምባሲዎች የዘመቻው መጀመርን አስመልክቶ መረጃ እንዲደረሳቸው መደረጉን የሳውዲ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው መመሪያው የሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበዋል። በዚሁ የሳውዲ እርምጃን ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ተመላስ እንደሚሆኑ የታወቀ ነገር የለም።