አዲስ አበባ ውስጥ መስማትና መናገር የማትችል ወጣት በፖሊስ ተደፈረች

የካቲት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ደብረ ብርሀን ብሎግ ስፖት በድምጽ በማስደገፍ ይፋ እንዳደረገው ዜና በአዲስ አበባ ጎዳና  ላይ መስማት የተሳናትና ዝግመት ያለባት ታዳጊ ወጣት ብቻዋን መንገድ ላይ ስትጓዝና መሄጃ ጥፍቷት ስትደናገር አንድ ግለሰብ ያገኛታል።

ግለሰቡም፦ ይቺ ልጅ ትንሽ ከመሸ ጥቃት ይደርስባታል ብሎ በማሰብ ከሌሎች ሰዎች ጋራ በመሆን  በ አቅራቢያው ወደሚገኝ  ፖሊስ ጣቢያ ይወስዳታል።

በአደራ የተረከበው  ፖሊስ “ነገ ቤተሰቦቿ ጋር እስከምናገኛት ድረስ እዚህ ትቆይ”በማለት ማረፊያ ቤት ያሳድሯታል።

ይሁንና ጥቃት እንዳይደርስባት  ይጠብቃት ዘንድ  በአደራ የተቀበላት ፖሊስ  ለአደራ ሳይበቃ ራሱ ጥቃት ፈጽሞባታል።  ድረ-ገጹ እንዳለው ሌሊት ላይ የእለቱ ተረኛ የነበረው ፖሊስ ዘገየ ደርሶ ሺፈራው የተባለው ፖሊስ ሁለት ጊዜ ሱሪዋን አስወልቆ ደፍሯታል።

ንጋት ላይ ተረኛ ፖሊሶች ወደ ምድብ ሥራቸው ሢሰማሩ መስማትና መናገር የማትችለው ወጣት በምልክት የሆነችውን ሁሉ ከተናገረች በሁዋላ ድርጊቱን የፈጸመባትን ፖሊስ በእጇ ጠቆመች።

ተጠርጣሪው ፖሊስ ሞላ ዘገዬ በፖሊስ ምርመራ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ብሎ ቢክድም ፤ በታዳጊዋ ላይ የመድፈር ወንጀል ለመፈፀሙ በሀኪም ማስረጃ ስለተረጋገጠበት  በ አቃቂ ቃሊቲ ፍትህ ጽህፈት ቤት አቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበታል።

ጉዳዩን ሲከታተለው የነበረው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም  መስማትና መናገር የተሳናትን ታዳጊ ወጣት በደፈረው  በፖሊስ ዘገዬ ደርሶ ሽፈራው ላይ የ 3 ዓመት ከ 7 ወር እስራት በይኗል።