ሐምሌ ፪( ሁለት )ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና :-የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እንደሚሆኑ አስቀድሞ ሲነገርላቸው የነበሩት የቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ
አቶ ድሪባ ኩማ የአስተዳደሩን ኃላፊነታቸውን ከአቶ ኩማ እጅ ተረክበዋል፡፡ በተለይ ሪፖርተር ጋዜጣ የምክትል
ከንቲባነት ሥልጣን እንደሚይዙ የተነበየላቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን እንደተገመተው ወደስልጣኑ ያልመጡ ሲሆን
በምክትል ከንቲባነት የቀድሞ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ተሹመዋል፡፡
ዛሬ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በተከናወነው ሥነሥርዓት ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ የካቢኔ አባሎቻቸውን
ሹመት ለም/ቤቱ አቅርበው ያስጸደቁ ሲሆን አባላቱም ቃለመሃላ ፈጽመዋል፡፡
የኩማ አስተዳዳር በሙስና በብልሹ አስተዳደር በተደጋጋሚ የሚተች ሲሆን ይህንንም ለመፍታት ያደረገው ጥረት የተሳካ
እንዳልነበር አቶ ኩማ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት የመጨረሻ ጉባዔ ላይ በይፋ አምነዋል፡፡ መቶ በመቶ በኢህአዴግ
አባላት የተያዘው አዲሱ ም/ቤት የጉልቻ ለውጥ ካልሆነ በስተቀር ከአቶ ኩማ ደመቅሳ ብዙም የተለየ ሥራ ያከናውናል
ተብሎ አይጠበቅም፡፡
በካቢኔ ሽግሽጉም ሆነ በአዲስ አበባ መስተዳድሩ ሹመት በአመዛኙ የተካተቱት ነባር የ ኢህአዴግ ካድሬዎች ናቸው።
ቀደም ባሉት ዓመታት የ አማራ ብሄራዊ ክልል ብዙሀን መገናኛ ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ የነበሩትና ከዚያም የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ ድንገት በመስተዳድሩ በተካሄደው ግምገማ እነ አቶ ከፍያለው አዘዘ ሲባረሩ ከ ኢቲቪ ተነስተው በመስተዳድሩ የተመደቡት አቶ ታቦር ገብረመድህን-በ አዲሱ ሹመትም የመስተዳድሩ አፈ ጉባዔ ሆነው እንዲቀጥሉ ሲደረግ፤ የህወሀቱ አቶ ወልደገብርኤል አብርሃ ደግሞ በምክትል አፈጉባኤነት ተመድበዋል ።
የህወሀቶቹ አቶ ሀይሌ ፍሰሃ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ፣ አቶ ይስሃቅ ግርማይ ደግሞ የአቅም ግንባታ ቢሮ ሀላፊ ሆነው ተመድበዋል።
ኢህአዴግ አዲስ አበባ በገባ ሰሞን በ ኢአዴግ የ አዲስ አበባ ሴቶች ሀላፊ፣ሁዋላ ላይ ደግሞ “ማህቶት’የተሰኘው የብአዴን ልሳን ዋና አዘጋጅ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት የብአዴኗ ወይዘሮ ፍሬህይወት አያሌው ደግሞ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ በመሆን በ አዲሱ ከንቲባ ተሹመዋል ።
ከንቲባው በመቀጠልም አቶ ጌታቸው ሀይለማርያምን የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ሀላፊ፣አቶ ጥላሁን ወርቁን የጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ሀላፊ፣አቶ ገብረ ፃዲቅ ሀጎስን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ፣ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረትን የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ፣ አቶ ኤፍሬም ግዛውን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ፣አቶ ሺሰማ ገብረስላሴን የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ፣አቶ ፎርኢኖ ፎላን የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሀላፊ፣አቶ ሰለሞን ሀይሌን የመሬት ማኔጅመንትና ልማት ቢሮ ሀላፊ፣አቶ ዲላሞ ኦቶሬን የትምህርት ቢሮ ሀላፊ እና አቶ ፀጋዬ ሀይለማርያምን የፍትህ ቢሮ ሀላፊ በማድረግ ሹመዋል።
ሹመቱ በ አመዛኙ በ ኢህአዴግ ነባር አባላት መካከል የ እርስ በርስ የቦታ ሽግሽግ መሆኑ “መተካካት” የተሰኘውን የ ኢህአዴግ ቋንቋ ቀልድነት ያሳየ ከመሆኑም ባሻገር ለእህል ውሃ እና ለሹመት ብለው ድርጅቱን የተጠጉትን አዳዲስ አባላት ጭምር ተስፋ ያስቆረጠ እንደሚሆን ዜናውን የሰሙ ወገኖች አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።